ሕዝቡ በሰላም፣ በአንድነትና በልማት ላይ በማተኮር እጅ ለእጅ ተያይዞ መስራት አለበት -ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

ነቀምት ፤ ሚያዚያ 30/2016 (ኢዜአ)፡- ሕዝቡ በሰላም፣ በአንድነትና በልማት ላይ በማተኮር እጅ ለእጅ ተያይዞ መስራት አለበት ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር  ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

በነቀምቴ ከተማ ወለጋ ስታዲየም የለውጡን መንግስት የሚደግፍ''ወለጋ የሰላምና የብልጽግና ምድር'' በሚል መሪ ሀሳብ ከአራቱ የወለጋ ዞኖች ነዋሪዎች የተሳተፉበት ሰልፍ ተካሂዷል።

በስፍራው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ እንዲሁም የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳን ጨምሮ የፌዴራልና የክልሉ ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች ተገኝተዋል።

በዚሁ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶር)፣  ህዝቡ በሰላም፣ በአንድነትና በልማት ላይ እንዲያተኩር ጥሪ አቅርበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ሕዝቡ ሰላሙን በማጽናት አሁን እጅ ለእጅ በመያያዝ ሀገራችንን ማልማት አለብን ብለዋል። 

ከሁሉም በላይ ለልማት፣ የተለያየ ሀሳብ ለማመንጨት አንድነት እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመው፤ ትውልዱን የሚጎዳ ነገር ከማድረግ በመቆጠብ በመመካከር አንድነትን ማጽናት ይገባል ብለዋል።

ከኢኮኖሚ አኳያ ከለውጡ በፊት ብዙ ችግር ተደቅኖ እንደነበር ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከለውጡ በኋላ ግን በብዙ ችግሮች ውስጥ ትልቅ የኦኮኖሚ ለውጥ እየተመዘገበ መሆኑን አብራርተዋል።

በለውጡ ዓመታት በተሰራ ስራ ግብርናንና ከተማን የሚለውጥ፣ ሀገር የሚያሻግር ኢኮኖሚ እየተመዘገበ መሆኑን አስረድተዋል።

"የጀመርነውን ስራ ከግብ ለማድረስ የሚያስቆመን ሀይል አይኖረም፣ በንጹህ ልባችን ሀገር ለመለወጥ ነው እየሰራን ያለነው'' ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ''አሁንም እንደ ትናንቱ በሙሉ ልብ እናገራለሁ። የኢትዮጵያን ብልጽግና እናረጋግጣለን፣ አንድነቷም ይጠበቃል፣ በአፍሪካ የምትከበር ሀገር ትሆናለች" ብለዋል።

ልማትና እድገታችንን የሚያፋጥን ሰላም እንዲጸና መትጋት እንደሚገባ ለሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ መግለጽ እፈልጋለሁ ሲሉም ተናግረዋል።

ወለጋን መቀየር እንፈልጋለን፣ እቅዳችን በጠላት ዓላማ እንዳይደናቀፍ ህዝባችን ከጎናችን መቆም ይገባዋል ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ሰልፉ ላይ ''ለውጡን እናጸናለን''፣ ''በሰላምም፣ በልማትም ምሳሌ ሆነን እናኮራዎታለን''፣ ''ሁሉንም አይነት ጽንፈኝነት እናወግዛለን'' የሚሉና ሌሎች መልዕክቶች ተደምጠዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም