የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከመጪው መስከረም ወር ጀምሮ የፕሮፌሽናል ሰርተፊኬት መርሐ ግብር ሊጀምር ነው

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 30/2016(ኢዜአ)፡- የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከመጪው መስከረም ወር ጀምሮ የፕሮፌሽናል ሰርተፊኬት መርሐ ግብር ሊጀምር ነው።

የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ጀይሉ ዑመር በሰጡት መግለጫ፤ ራስ ገዝ የሆነው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፕሮፌሽናል ሰርተፊኬት መርሐ ግብር (Professional Certification Program) ሊጀምር መሆኑን ገልፀዋል።

ፕሮግራሙ ከሚቀጥለው ዓመት መስከረም ወር ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚደረግ ተናግረዋል። 

ዩኒቨርሲቲውን በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ወደ ሙሉ ራስ ገዝ ለማስገባት በርካታ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸው በተለይም የሀገሪቱን ፍላጎት ያማከለ የትምህርት ተቋም ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል። 

ዩኒቨርሲቲው ራስ ገዝ የሚያሰኘውን በርካታ ሪፎርም እያከናወነ እንደሆነም አመልክተዋል።

በዚህም በተለያዩ ሙያዎች ውስጥ የሚገኙ እንዲሁም በቅደመ ምረቃና ድህረ ምረቃ ትምህርት ፕሮግራሞች ተመርቀው ኢንዱስትሪ ውስጥ ለሚገቡ ተመራቂዎች ራሱን የቻለ የፕሮፌሽናል ሰርተፊኬት መርሐ ግብር መስጠት ለመጀመር መወሰኑን ነው ያነሱት።

ፕሮግራሙ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀና የገበያውን ፍላጎት መሰረት ያደረገ ሲሆን መርኃ ግብሩ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚሰጥ እንደሆነም አስታውቀዋል ።

የፕሮግራሙ መጀመር በስራ ገበያው ውስጥ ብቁ ሙያተኞችን ለማግኘትና የዩኒቨርስቲውን አቅምና ብቃት ያለው ባለሙያ የማፍራት ተልዕኮ የሚያሳካ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ዶክተር ጀይሉ አያይዘውም የፕሮፌሽናል ሰርተፊኬት መርሐ ግብር በሁሉም ዘርፎች ላይ እንደሚሰጥ ጠቁመው፣ ይህ የሚመራበት አሰራር ይዘረጋል ብለዋል።

በስራ ገበያ ያሉ ሙያተኞችም ሆኑ በትምህርት ስርዓት ውስጥ ያሉ ተማሪዎች ፕሮፌሽናል ሰርትፊኬት መውሰድ እንደሚችሉ ተገልጿል።

ፕሮፌሽናል ሰርተፍኬቱ የገበያውን ፍላጎት መሰረት ያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለፕሮግራሙ ትግበራም ከባለድርሻ ተቋማት ጋር በትብብር እንደሚሰራ ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም