በሐረሪ ክልል የአካባቢ ብክለትን የሚያስከትሉ ተጽዕኖዎችን ለመከላከል እየተከናወኑ የሚገኙ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ

ሐረር፤ ሚያዚያ 30/2016(ኢዜአ)፡- በሐረሪ ክልል የአካባቢ ብክለትን የሚያስከትሉ ተጽዕኖዎችን ለመከላከል እየተከናወኑ የሚገኙ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ሲሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ አስታወቁ።

"ብክለት ይብቃ! ውበት ይንቃ!" በሚል መሪ ሀሳብ በሀረሪ ክልል ለስድስት ወራት የሚተገበር የአካባቢ ብክለትን የመከላከል የንቅናቄ መርሃ ግብር ዛሬ በይፋ ተጀምሯል።


 

ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን እንደገለጹት የአካባቢ ብክለት በሰው ልጅ ጤና ላይ ከሚያደርሰው ጉዳት በተጨማሪ በእንስሳትና እጽዋት ላይ ከፍተኛ ጉዳትያስከትላል።

የአካባቢ ብክለት በአየር፣ በውሃ፣ በአፈርና በሌሎችም የተፈጥሮ ሀብቶች ላይ እያደረሰ ያለውን ጉዳት ለመከላከል በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በተጠነሰሰው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አመርቂ ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።

በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በተከታታይ አመታት የተተከሉ ችግኞች በአካባቢ ጥበቃ ረገድ ውጤት እየተገኘባቸው መሆኑን ጠቅሰዋል።

ይሁን እንጂ የፕላስቲክ ቆሻሻ በሚያደርሰው የአፈር ለምነት መቀነስ፣ ምርትና ምርታማነትን ለማጎልበትና የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ በሚከናወኑ ስራዎች ላይ ተግዳሮት እየሆነ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

በክልሉ የፕላስቲክ ብክለት የሚያስከትሉት ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑ ምርቶቹን መልሶ ጥቅም ላይ በማዋል የጉዳት መጠኑን ለመቀነስ "ኪዩቤክ" ከተባለ ድርጅት ጋር ስምምነት ተደርሶ ወደ ስራ መገባቱን ገልጸዋል።

የደረቅና ፈሳሽ ቆሻሻን በአግባቡ ከማስወገድ አንፃርም የተጠናከረ ስራ እንደሚሰራ ጠቁመው ለንቅናቄው ስኬታማነትም ሁሉም በአርበኝነት ስሜት በመስራት ለሚቀጥለው ትውልድ እዳን ሳይሆን ምንዳን ማውረስ ያስፈልጋል ሲሉ ተናግረዋል።

የፌዴራል አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ተሾመ አቡኔ በወቅቱ እንዳሉት መርሃ ግብሩ በአየር ንብረት ለውጥ ችግር ምክንያት እየተራቆተ የሚገኘውን የተፈጥሮ ሀብት መመናመን በመቀነስ በኩል ከፍተኛ እምርታ እያሳየ ነው።

መርሃ ግብሩን በተለያዩ አጋዥ የንቅናቄ ስራዎች ማገዝና ውጤቱን ማጽናት ትኩረት የተሰጠው ሀገራዊ ተግባር መሆኑን አመልክተዋል።

የክልሉ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ስራ አስኪያጅ አቶ ሰሚር በክሪ በበኩላቸው በንቅናቄው የክልሉ ሕዝብ በአካባቢ ብክለት ዙሪያ በቂ ግንዛቤ በመያዝ ድርሻውን እንዲወጣ ለማድረግ ዝግጅት መደረጉን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም