ቀጥታ፡

የታላቁ አል ነጃሺ 00 መንደር ግንባታ በእስልምና ታሪክ ስሟ በጉልህ የሚጠቀሰውን ኢትዮጵያን ለዓለም የሚያስተዋውቅ ነው

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 30/2016(ኢዜአ)፡- የታላቁ አል ነጃሺ 00  መንደር ግንባታ በእስልምና ታሪክ ስሟ በጉልህ የሚጠቀሰውን ኢትዮጵያን ለዓለም የሚያስተዋውቅ መሆኑን የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ገለጸ።

በኢትዮጵያ እስልምና የተጀመረበትን፣ የታሪኩን መነሻና መገኛ ለመጠቆም ታላቁ አል-ነጃሺ 00  መንደር ግንባታ  የጅማሮው ማብሰሪያ መርሀ ግብርም በአዲስ አበባ ተካሂዷል።


 

የመድረኩ አላማም የቦታውን ታላቅነት በማሰብ በፕሮጀክቱ ላይ ሁሉም በቻለው አቅም ሁሉ ርብርብ እንዲያደርግ ለማብሰር መሆኑ ተገልጿል።

በመንደሩ የተለያዩ ንዑስ ፕሮጀከቶች የታሰቡ ሲሆን የሙዚየም፣ ሃላል ሆቴሎችና ሎጆች፣ የአምልኮ ስፍራዎችና የጥናትና ምርምር ተቋማት የሚገነቡ ይሆናል።፡

ከዚህም በተጨማሪ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ ሌሎች የትምህርት ተቋማት፣ የህክምና ተቋማት፣ የስፖርት ማዘውተሪያና የመሰብሰብያ አዳራሾች የሚሰሩ ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የታሪክና ቅርስ ዘርፍ ሃላፊ ሸህ መሀመድ አሚን፤ የፕሮጀክቱ አላማ በእስልምና ትልቅ ስፍራ ከሚሰጠው ከመካና መዲና ቀጥሎ ስሟ በጉልህ የሚጠቀሰውን ኢትዮጵያንና እሴቶቿን ለዓለም ለማስተዋወቅ ነው ብለዋል።

በመሆኑም የነጃሺ መካነ ቅርስ አሻራ ባለበት ትግራይ ክልል ውቅሮ ከተማ ታሪኩን በሚመጥን መልኩ የታላቁ የአል ነጃሺ 00  መንደር ግንባታ የሚከናወን መሆኑን ገልጸዋል።


 

የትግራይ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዝደንት ሸህ አደም አብዱልቃድር፤ የፕሮጀክቱ አዓላማ ጥልቅና ሀገርን የሚያኮራ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም ለስኬቱ የሁላችንም ድጋፍና ርብርብ አስፈላጊ ነው ሲሉ ተናግረዋል። 

የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አብዱልሀዲ መሀመድ፤ የፕሮጀክቱ ግንባታ ታሪኩን በሚመጥን መልኩ በተለያዩ አካላት ትብብር የሚከናወን መሆኑን ገልጸዋል።


 

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳ በበይነ መረብ ባስተላለፉት መልእክት ፕሮጀክቱን ላቀዱና ላነሳሱ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።

በመሆኑም ለስኬታማነቱ የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍና እገዛ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሸህ ሃጂ ኢብራሂም ቱፋ፣ የፌደራል እና የክልሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችና ኡለማዎች በመድረኩ ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም