ሀገራዊ የከተሞች የጽዳት እና አረንጓዴ ልማት ስራዎች ንቅናቄ በይፋ ተጀመረ

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 30/2016(ኢዜአ)፦ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚካሄደው የከተሞች የጽዳት እና አረንጓዴ ልማት ስራዎች ሀገራዊ ንቅናቄ በይፋ ተጀመረ።

የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚካሄደውን የከተሞች የጽዳት እና አረንጓዴ ልማት ስራዎች ሀገራዊ ንቅናቄ "ጽዱ ከተሞች ለኢትዮጵያ ከፍታ" በሚል መሪ ሀሳብ ዛሬ በይፋ አስጀምሯል።

በመርኃ ግብሩ ላይ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ እና ብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አደም ፋራህ፣ የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒን ጨምሮ ሚኒስትሮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ በዚሁ ወቅት ፤ንቅናቄው በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይፋ የተደረገው የ"ጽዱ ጎዳና- ኑሮ በጤና" ንቅናቄ አካል ነው ብለዋል።

ንቅናቄው ዘመናዊ የቆሻሻ አወጋገድ ስርዓትን እውን በማድረግ ጤናማ ህብረተሰብ ለመፍጠር  የሚያስችል  መሆኑን ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ ይፋ የተደረገው ንቅናቄ በቀጣይ ወደ ሌሎች ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች እንደሚሰፋ ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም