ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በድሬዳዋ ተጨባጭ ውጤቶች እየተመዘገቡ ነው - ከንቲባ ከድር ጁሃር

ድሬዳዋ፤ ሚያዝያ 30/2016 (ኢዜአ)፡- በድሬዳዋ አስተዳደር የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ለኢንዱስትሪው ዘርፍ በተደረገ ድጋፍ እና ክትትል ተጨባጭ ውጤቶች እየተመዘገቡ መሆኑን ከንቲባ ከድር ጁሃር ገለጹ።

በንቅናቄው የተዘጉ ፋብሪካዎች ወደ ማምረት ተመልሰው ስድስት ሺህ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠራቸውንም አመልክተዋል።

ከንቲባ ከድር ጁሃር ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ለማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የመሬት አቅርቦት ከማመቻቸት ባለፈ ከፋይናንስ እና ከህግ አኳያ የነበሩ ክፍተቶች በተደረገው የተቀናጀ ድጋፍና ክትትል መፍታት ተችሏል።

እንዲሁም በተሰጡ ፈጣንና ቀልጣፋ የአንድ ማዕከል አገልግሎቶች ተጨባጭ ውጤቶች ተመዝግበዋል ብለዋል።

እነዚህን ማበረታቻዎችና ልዩ ድጋፎች በመጠቀም ተዘግተው የቆዩ ሰባት የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች ወደ ማምረት ተመልሰው ምርት እያሳደጉ ይገኛሉ ብለዋል።

እነዚህ ፋብሪካዎች ከስድስት ሺህ በላይ ለሆኑ ዜጎች ቋሚና ጊዚያዊ የስራ ዕድል ከመፍጠር በተጨማሪ ተኪ ምርቶችን በማምረት የውጭ ምንዛሪን እያስቀሩ መሆናቸውን ነው ያወሱት።

እንደ ከንቲባ ከድር ገለፃ፤ እየተደረጉ በሚገኙ ማበረታቻዎች የተነቃቁ አዳዲስ ባለሃብቶች በብዛት ወደ ዘርፉ እየተቀላቀሉ ነው።

ሀገራዊ የለውጥ አመራር ከመጣ እና ንቅናቄው ከተጀመረ ወዲህ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ላይ በተከናወኑ ተግባራት በኢንቨስትመንት ስራ የሚሰማሩ የውጭና የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች ቁጥር በዕጥፍ መጨመሩን ጠቅሰዋል።

ባለፉት ስድስት ዓመታት ወደ ስራ የተሸጋገሩ ኢንዱስትሪዎች የውጭ ምንዛሬን ከማስገኘት ባለፈ ከ16ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠራቸውን ተናግረዋል።

እነዚህን ተጨባጭ ውጤቶች ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስና በኢትዮጵያ ታምርት የተገኙ ውጤቶችን ለማሳደግ በቀጣይ የተሻለ ስራ ይከናወናል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም