ቀጥታ፡

የ''ኢትዮጵያ ታምርት'' ንቅናቄ በቤኒሻንጉል ጉሙዝና ጋምቤላ ክልሎች ኢንዱስትሪዎችን አነቃቅቷል

አሶሳ/ጋምቤላ ፤ሚያዝያ 30/2016 (ኢዜአ)፦ የ''ኢትዮጵያ ታምርት'' ንቅናቄ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና በጋምቤላ ክልሎች ኢንዱስትሪዎችን ከማነቃቃት ባለፈ ሕዝቡን ተጠቃሚ ማድረጉን የክልሎቹ ርዕሳነ መስተዳድሮች ገለጹ።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሐሰን ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዳስታወቁት፤ የ''ኢትዮጵያ ታምርት'' ንቅናቄ በክልሉ ከአነስተኛ ኢንተርፕራይዞች እስከ ትላልቅ ፋብሪካዎች ተከፍተው ወደ ምርት እንዲገቡ አድርጓል፡፡

የዱቄት፣ የሳሙናና የእምነበረድ እንዲሁም የመኖ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች፣ ቀርከሃን በመጠቀም የተለያዩ የቤት ቁሳቁስ የሚያመርቱ ኢንተርፕራይዞችን ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡

የ''ኢትዮጵያ ታምርት'' ንቅናቄ በሃይል አቅርቦትና በሌሎችም ችግሮች ተዘግተው የቆዩ ኢንተርፕራይዞችና ፋብሪካዎችን ወደ ምርት ለመመለስ መቻሉንም አቶ አሻድሊ ገልጸዋል፡፡

በዚህም ለኅብረተሰቡ ምግብና ሸቀጣ ሸቀጦችን በተመጣጣኝ ዋጋ ከማቅረብ ባለፈ ፍላጎትና አቅርቦትን ለማሟላት እያስቻለ መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ አስረድተዋል፡፡

በተጨማሪም ኢንተርፕራይዞችና ፋብሪካዎቹ እያንዳንዳቸው እስከ 300 ለሚደርሱ ሰዎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል መፍጠራቸውን አስታውቀዋል።

በክልሉ የሚታየው የኢንዱስትሪ እንቅስቃሴ ከአገራዊ ለውጡ በኋላ በክልሉ ከተመዘገቡ ለውጦች እንደ አንዱ እንደሚጠቀስ የተናገሩት አቶ አሻድሊ፤ ይህም "የክልሉን ሕዝብ ሕይወት ለመለወጥ እያስቻለ ነው" ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄው የተነቃቁት ፋብሪካዎችና አምራች ኢንተርፕራይዞችን ምርት የመጠቀሙም ሂደት ከዚሁ ጋር በትኩረት እንደሚቀጥል የገለጹት አቶ አሻድሊ፤ የሁሉም በአገሩ ምርት መኩራት ለአገራዊ እድገቱ ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።

በክልሉ የ'ኢትዮጵያ ታምርት' ንቅናቄ ስኬታማነት በተለይም የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ድጋፍና ክትትል በማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉን ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል።

የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በበኩላቸው እንዳስታወቁት፤ በጋምቤላም "ኢትዮጵያ ታምርት" በሚል መሪ ሐሳብ የተጀመረው ንቅናቄ በክልሉ የኢንዱስትሪ ልማት ከፍተኛ መነቃቃት ፈጥሯል።

ርዕሰ መስተዳድሩ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት፤ ለኢትዮጵያ አገር በቀል ኢኮኖሚ ተደጋግፈው ለውጥ ያመጣሉ ተብለው ከተለዩት አምስት የብዝሃ ኢኮኖሚ ዘርፎች መካከል ኢንዱስትሪ አንዱ ነው።

ቀደም ሲል በክልሉ የኢንዱስትሪ ልማቱ ብዙ ያልሰፋ መሆኑን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ "የኢትዮጵያ ታምርት" ንቅናቄ ከተጀመረ ወዲህ በዘርፉ ከፍተኛ መነቃቃት መፈጠሩን ጠቁመዋል።

የክልሉ መንግስት ለአምራች ኢንዱስትሪው በሰጠው ልዩ የድጋፍና ክትትል ስራም ምርታማነትን ከማሳደግ ባለፈ በዘርፉ የሚሰሩ ባለሃብቶች ቁጥር እንዲጨምሩ በማድረግ ረገድ ተጨባጭ ለውጤቶች መመዝገገባቸውን ተናግረዋል።

የኢንዱስትሪው ዘርፍ ማደግ ከውጪ የሚገቡ ተኪ ምርቶችን በማምረት የውጪ ምንዛሬን ከማስቀረት ባለፈ በስራ እድል ፈጠራም የማይተካ ሚና እንዳለው አስረድተዋል።

በመሆኑም ኢንዱስትሪው ያለውን ጠቀሜታ ግምት ውስጥ በማስገባት የክልሉ መንግስት ዘርፉን ለማሳደግ በልዩ ትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም