የጤና ተቋማትን ንጽህና መጠበቅ ከንቅናቄ ባሻገር የዘወትር ተግባር መሆን አለበት -ዶክተር መቅደስ ዳባ

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 29/2016(ኢዜአ)፦ የጤና ተቋማትን ንጽህናን መጠበቅ ከንቅናቄ ባሻገር የዘወትር  ተግባር  ሊሆን እንደሚገባ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ተናገሩ፡፡

ሚኒስትሯ የ "ጽዱ ጎዳና-ኑሮ በጤና" ንቅናቄ አካል የሆነውን ጽዱ የጤና ተቋማትና አካባቢን የመፍጠር ንቅናቄ በአለርት ኮምፕሬሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል እና በጴጥሮስ ጻውሎስ ሆስፒታል ተገኝተው በይፋ አስጀምረዋል።


 

ዶክተር መቅደስ ዳባ ንቅናቄውን ባስጀመሩበት ወቅት ፤ የንጽህና ጉድለት ኢትዮጵያን ጨምሮ የታዳጊ አገራት የጤና እክል መንስኤ መሆኑን በመጥቀስ የንጽህና ጉድለት ከሚስተዋልባቸው ስፍራዎች መካከል ደግሞ የጤና ተቋማት ይገኙበታል ብለዋል።

እኤአ በ 2019 በተደረገ ጥናት በሆስፒታል ተወልደው በኢንፌክሽን ከሚጠቁ ህጻናት መካከል 56 በመቶው በንጽህና ጉድለት የሚጠቁ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ችግሩን ማስቀረት የሚቻለው ምቹ እና ንጽህናው የተጠበቀ የጤና ተቋም በመፍጠር ብቻ ነው ብለዋል፡፡

ይፋ የተደረገው ንቅናቄ በህጻናትና እናቶች ላይ የሚከሰተውን የጤና እክል ለመቀነስ የጎላ ሚና እንደሚኖረው አመላከተዋል።

ሚኒስቴሩ በጤናው ዘርፍ የሚተገበሩ መስፈርቶችን በመጠበቅ የላቀ ፈጻሚ ሆኖ ለመገኘት በርካታ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

ንጽህናው የተጠበቀ አካባቢን ለመፍጠር ስራው ከንቅናቄ ባሻገር የዘወትር ተግባር ሊሆን እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡


 

የቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ዋና ስራ አስኪያጅ ዶክተር አብርሃም እሸቱ በበኩላቸው፤የአካባቢ ንጽህናን መጠበቅ ቅንጦት ሳይሆን ግዴታ ነው ብለዋል፡፡

ሆስፒታሉ ለታካሚዎቹና ሰራተኞቹ ምቹና ጽዱ አካባቢን ለመፈጠር የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡


 

በንቅናቄው መታጠቢያ ቤቶች፣ የታካሚ ማቆያና ሽንት ቤቶችን የማስዋብ እንዲሁም አዳዲስ ግንባታዎች ለማካሔድ ዝግጅት መደረጉን የተናገሩት ደግሞ የአለርት ኮምፕሬሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ዋና ስራ አስኪያጅ ዶክተር ሽመልስ ገዛኽኝ ናቸው።


 

ዶክተር መቅደስ ዳባ በሆስፒታሎቹ አዳዲስ መጸዳጃ ቤቶችን ለመገንባት የሚያስችል የመሰረት ድንጋይ አስቀምጠዋል፡፡

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም