የኢትዮጵያ ደምና ህብረ-ህዋስ ባንክ አገልግሎትና የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በጋራ ለመስራት ተፈራረሙ

አዲስ አበባ ፤ ሚያዚያ 29 /2016 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ደምና ህብረ-ህዋስ ባንክ አገልግሎትና የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ።

ከነገ ጀምሮ እስከ ግንቦት 8 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ "ደሜን እለግሳለሁ ደስታውም ሽልማቴ ነው" በሚል መሪ ሃሳብ  የደም ልገሳ መርኃ ግብር በአዲስ አበባ እንደሚጀመር  ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ደምና ህብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አሸናፊ ታዘበው (ዶ/ር)ና የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ምክትል ዋና ፀሃፊ አቶ አበራ ሉሌሳ ስምምነቱን ተፈራርመዋል።

ስምምነቱ የበጎ ፍቃደኛ ደም ለጋሾችን ቁጥር በማሳደግና በማስተባበር የሚፈለገውን ደም ለመሰብሰብ አላማ ያደረገ እንደሆነ ተገልጿል።

የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር አሸናፊ ታዘበው (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት አገልግሎቱ 48 ቅርጫፎችን በመክፈትና አሰራሩን በቴክኖሎጂ በማዘመን በቂ  ደም ለመሰብሰብ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው።


 

ስምምነቱ ሁለቱ ተቋማት የሚሰሩትን የበጎ ፍቃድና የሰብዓዊነት ስራ ይበልጥ ለማጠናከር ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለው ተናግረዋል።

በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች በመንቀሳቀስና በጎ ፍቃደኛ ደም ለጋሾችን በማስተባበር የሚፈለገውን ደም ለመሰብሰብ  እንደሚያግዝ ተናግረዋል። 

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ምክትል ዋና ፀሃፊ አቶ አበራ ሉሌሳ በበኩላቸው የቀይ መስቀል ማህበር በተፈጥሮና በሰው ሰራሽ አደጋ ጉዳት የሚደርስባቸውን ዜጎች የመደግፍና መልሶ የማቋቋም ስራውን አጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል። 


 

የኢትዮጵያ ደምና ህብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት የሚሰራው ሰብዓዊ ስራ ከተቋማቸው ጋር የሚገናኝ በመሆኑ አብረው ለመስራት መስማማታቸውን ገልፀዋል።

ማህበሩ በጎ ፍቃደኞ ደም ለጋሾች  በንቃት እንዲሳተፉ እንዲሁም በቂ የሆነ ደም በመሰብሰብ የሰውን ህይወት ለመታደግ  አበክረው እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

የቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ በዓልን ምክንያት በማድረግ ከነገ ጀምሮ እስከ ግንቦት 8 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ "ደሜን እለግሳለሁ ደስታውም ሽልማቴ ነው" በሚል መሪ ሃሳብ  የደም ልገሳ መርኃ ግብር በአዲስ አበባ እንደሚጀመር  ተገልጿል።

የደም ልገሳ መርኃ ግብሩ በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች እንደሚካሄድ ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም