የታላቁ አል-ነጃሺ 00 መንደር ጅማሮ ማብሰሪያ እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ ፤ ሚያዚያ 29 /2016 (ኢዜአ)፦የታላቁ አል-ነጃሺ 00 መንደር ጅማሮ ማብሰሪያ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሸህ ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ፣ የትግራይ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሸህ አደም አብዱልቃድር ተገኝተዋል፡፡

እንዲሁም የፌደሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ዘሀራ ሁመድ ፣የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የማህበራዊ ልማት ሴክሬተርያት ካቢኔ ሀላፊ ፕሮፌሰር ክንድያ ገብረህይወትና ከፍተኛ የፌዴራልና የክልሎች የመንግስት የስራ ሀላፊዎች ታድመዋል።

በመርሀ ግብሩ የታላቁ አል-ነጃሺን ታሪካዊ ዳራ የሚያስቃኝ ዶክመንተሪ ፊልም ለእይታ ቀርቧል።

የመድረኩ አላማ አልነጃሺን ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ለአለም ማስተዋወቅ መሆኑ ተመላክቷል።

የዜሮ ዜሮ መጠርያ ሃሳቡ የመነጨው ከሸህ ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ ሲሆን መነሻ ሃሳቡ እስልምና በኢትዮጵያ የተጀመረበትንና የታሪኩን መነሻና መገኛ ለመጠቆም መሆኑ ተመላክቷል፡፡ 

ፕሮጀክቱ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት  ፣ የትግራይ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት እንዲሁም የአልነጃሺ መልሶ ግንባታና ልማት ኢኒሸቲቭ በጋራ የሚያከናውኑት መሆኑ ተገልጿል

የፕሮጀክቱ አላማ በኢትዮጵያ ብሎም በአለም ትልቁ የሙስሊሞች ታሪክና ቅርሰ የሆነውንና ከመካ መዲና ቀጥሎ በአለም የእስልምና መገኛ በሆነችው ኢትዮጵያ የሚገኘውን ሃብት በስፋት ማስተዋወቅ ነው፡፡

በተጨማሪ በከባዱ ፈተና ወቅት ለሙስሊሞች ከለላ የሆኑት የነጃሺ መካነ ቅርስ አሻራ ባለበት በትግራይ ክልል ውቅሮ ከተማ ክብራቸውና ታሪካቸውን በሚመጥን መልኩ አለም አቀፍ የቱሪስት መዳረሻ እንዲሆን የሚያስችል ሁሉን አቀፍ የቱሪስት መንደር ለመገንባት ያለመ ነወ፡፡

በቱሪስት መንደሩ የተለያዩ ንዑስ ፕሮጀከቶች የታቀፉ ሲሆን ከነዚህም ደረጃውን የጠበቀ ሙዚየም፣ ሃላል ሆቴሎችና ሎጆች ፣የእምነት ስፍራዎች ፣ የጥናትና ምርምር ተቋማት እንደሚገነቡ ተመላክቷል፡፡

እንዲሁም ዩኒቨርሲቲ ፣የቴክኒከና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጆች ፣ኢንተርናሽናል ትምህርት ቤት ፣ደረጃቸውን የጠበቁ ሆስፒታሎችና የጤና ተቋማት ፣ለህዝብ አገልገሎት የሚውሉ የስፖርት ማዘውተርያ ስፍራዎችና መሰብሰብያ አዳራሾች እንደሚኖሩት ተመላክቷል።

መርኃ ግብሩ የተዘጋጀው ኢትዮጵያውያንና በአለም የሚኖሩ የታሪኩ ባለቤቶች የቦታውን ታላቅነት በማሰብ በፕሮጀክቱ ላይ በቻሉት አቅም ርብርብ እንዲያደርጉ  ለማብሰር መሆኑ ተገልጿል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም