የግሉ ዘርፍ በአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና ያለውን ሰፊ የገበያ እድል ለመጠቀም ራሱን ማዘጋጀት አለበት

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 29/2016 (ኢዜአ)፦ የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጠና የሚፈጥረውን ሰፊ የገበያ እድል ለመጠቀም የንግዱ ማህበረሰብ  ጥራት ያለው ምርትና አገልግሎት  ለማቅረብ ራሱን ማዘጋጀት እንዳለበት ተገለጸ።

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና በሚፈጥረው ዕድል የግሉ ዘርፍ ተጠቃሚ ለመሆን ያለውን ዝግጁነት በተመለከተ የፓናል ውይይት አካሂዷል።

በንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር የዓለም አቀፍና ቀጠናዊ ንግድ ትስስር መሪ ስራ አስፈጻሚ ታገስ ሙሉጌታ ኢትዮጵያ ለአህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጠናው እያደረገች ያለውን ዝግጅት አብራርተዋል።


 

ስምምነቱ ላይ በሚካሄዱ ድርድሮችና ስምምነቱን ለመተግበር በሚደረጉ ዝግጅቶች ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በዚህ ረገድ የንግዱ ማህበረሰብ የስምምነት ሂደቱን በተመለከተ በቂ ግንዛቤ በመያዝ፣ ቀጠናዊ ትስስርን በማጠናከር  ፣ ተአማኒነትን በማሳደግ ተወዳዳሪ ለመሆን ዝግጅት ማድረግ እንዳለበት አስገንዝበዋል።

እንደ መሪ ስራ አስፈጻሚው ገለጻ አግሮ ፉድ፣ የጨርቃጨርቅና የቆዳ ምርቶች በነጻ ንግድ ቀጠናው ተጠቃሚ ለመሆን ትልቅ አቅም ያላቸው ዘርፎች ናቸው።

በጉምሩክ ኮሚሽን የታሪፍና ስሪት አገር ዳይሬክተር ካሳዬ አየለ በበኩላቸው ለአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና ትግበራ በጉምሩክ ኮሚሽን በኩል ያለውን ቅድመ ዝግጅት አስረድተዋል።


 

ምርቶች በአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና የስሪት ሀገር ህግ መሰረት መመረታቸውን በማረጋገጥ ሰርተፍኬት ለመስጠት የሚያስችሉ ቅድመ ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት መሰንበት ሸንቁጤ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በአፍሪካ ውስጥ ያላት የወጪ ንግድ ድርሻ 20 በመቶ እንዲሁም የገቢ ንግድ ምጣኔው ከስድስት በመቶ እንደማይበልጥ ጠቅሰዋል።


 

ከዚህ አኳያ ነጻ የንግድ ቀጠናው የሀገሪቱን ንግድ በማሳደግ ሰፊ የገበያ እድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል።

በተጨማሪም የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ፣ ካፒታል ለመሳብ፣ የቴክኖሎጂና የሙያ ክህሎት በማሳደግ አማራጭ ምርቶችን በተሻለ ዋጋ ለተጠቃሚዎች ለማቅረብና ለስራ እድል ፈጠራ ጉልህ ሚና አለው ብለዋል፡፡

የንግዱን ማህበረሰብ ተወዳዳሪ ሊያደርጉት የሚችሉት ጥራት ያላቸው ምርትና አገልግሎቶች በመሆናቸው በዚሁ ረገድ የንግዱ ማህበረሰብ መዘጋጀት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

እንዲሁም በመንግስት በኩል ጠንካራ የቁጥጥር ስርአት መዘርጋት አስፈላጊ መሆኑን አክለዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ነጻ የንግድ ቀጠናው በሚያስገኘው እድል ለመጠቀም ራሳቸውን እያዘጋጁ መሆኑን ገልጸዋል።

የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጠና እአአ በ2021 ስራ ላይ እንዲውል የጸደቀ ስምምነት ሲሆን 3 ነጥብ 4 ትሪሊዮን ዶላር ገበያ ሊፈጥር እንደሚችል መረጃዎች ያሳያሉ።

 

 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም