በቀጣይ አራት አመታት 10 ሺህ ኪሎ ሜትር የገጠር መንገድ ለመገንባት እቅድ ተይዟል

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 29/2016 (ኢዜአ)፦  በቀጣይ አራት አመታት 10 ሺህ ኪሎ ሜትር የገጠር መንገድ ለመገንባት እቅድ መያዙን የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ ገለጹ።

የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ፤ በተለይም ሰፊ የግብርና ልማት በሚከናወንበት የገጠሩ አካባቢ የመንገድ መሰረተ ልማት አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

የገበያ ትስስር ለመፍጠርና የምርት አቅርቦትን ለማሳለጥ እንዲሁም ሌሎች የልማት ክንውኖችን ለማሳካትም መንገድ ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።

በገጠር ተደራሽነትና ትስስር ፕሮግራም የገጠር መንገድ ልማት የሚከናወን መሆኑን ጠቅሰው ለዚህም ከዓለም ባንክ 300 ሚሊየን ዶላር ተገኝቷል ብለዋል።

በመሆኑም በዓለም ባንክ ድጋፍ፣ በፌዴራል መንግስትና በክልሎች ትብብር በቀጣይ አራት አመታት 10 ሺህ ኪሎ ሜትር መንገድ የሚገነባ መሆኑን ገልጸዋል።

ለመንገድ ፕሮጀክቱ ክልሎች 30 በመቶ ተጨማሪ የበጀት ተሳትፎ እንዲኖራቸው የሚደረግ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የመንገድ ፕሮጀክቱ የምርት አቅርቦት ተደራሽነትን በማሳለጥና የገበያ ትስስርን በመፍጠር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እገዛ የሚኖረው መሆኑን ሚኒስትር ዴታው ገልጸዋል።

በገጠር ተደራሽነትና ትስስር ፕሮግራም መሰረት የሚከናወነው የመንገድ ልማት 128 ወረዳዎችን ከዋና መንገድ ጋር የሚያገናኝ ይሆናል።

በአገሪቷ ባለፉት ስድስት አመታት 5 ሺህ 500 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ መገንባቱን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም