በጋምቤላ ክልል በበጋ የመስኖ ልማት እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች የሚበረታቱ ናቸው - የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ

ጋምቤላ፤ ሚያዝያ 29/2016 (ኢዜአ)፦ በጋምቤላ ክልል በበጋ የመስኖ ልማት እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች የሚበረታቱ መሆናቸውን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ገለጹ። 

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በማጃንግ ዞን መንገሺ ወረዳ በበጋ መስኖ እየለማ ያለውን ስንዴና የሩዝ እርሻ ጎብኝተዋል። 


 

ርዕሰ መስተዳድሩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት በሀገር ደረጃ የስንዴና የሩዝ ልማት ልዩ ትኩረት ከተሰጣቸው የሰብል ዓይነቶች መካከል መሆናቸውን አስታውሰዋል።

ሰለሆነም በጋምቤላ ወይና ደጋ የአየር ንብረት ባለበት የማጃንግ ዞን ካለፈው ዓመት ጀምሮ በሙከራ ደረጃ  ሲከናወን የነበረ የስንዴና የሩዝ ልማት ውጤቱ እየታየበት መጥቷል ብለዋል። 

በዘንድሮው የበጋ ወቅትም በመንገሺ ወረዳ ብቻ ከ43 ሄክታር በላይ መሬት  በስንዴና በሩዝ  እንዲሸፈን መደረጉን ጠቅሰው፤ ውጤቱም አርሶ አደሩን ይበልጥ ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን አይተናል ብለዋል። 

የበጋ መስኖ ልማቱ የምግብ ዋስትናን በቤተሰብና በአካባቢው ደረጃ ለማረጋገጥ የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት የሚያስችል ለመሆኑም ማሳያ ነው ብለዋል ርዕሰ መስተዳድሩ። 


 

የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡጁሉ ሉዋል በበኩላቸው በክልሉ የስንዴንና የሩዝ ልማትን አርሶ አደሩ ዘንድ ለማስፋት የተደረገው ጥረት ውጤት አስገኝቷል ብለዋል። 

በተለይም አርሶ አደሮቹ በፊት በማይታወቅባቸው የስንዴና ሩዝ ልማት ዘርፍ በበጋ መስኖ ልማት ላይ ተሰማርተው ምርታማነታቸውን እያሳደጉ እንደሚገኙ ጠቅሰው፤ ክልሉም ለስንዴና ለሩዝ ልማት ምቹ አካባቢ መሆኑን በተደረጉ ሙከራዎች መረጋገጡን ተናግረዋል።

በመሆኑም በቀጣይ ጊዜያት አርሶ አደሩንና ባለሃብቱን በማስተባበር የስንዴና የሩዝ ልማቱን ለማስፋት እንደሚሰራም አብራርተዋል። 

በመስክ ጉብኝቱ ላይ የተገኙ  አርሶ አደሮች በሰጡት አስተያየት ካለፈው ዓመት ጀምረው ስንዴንና ሩዝን ማልማት መጀመራቸውን ገልፀዋል። 

በተለይም በሙከራ ደረጃ  የጀመሩት የስንዴ ምርት በመሸጥ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል። 

በዘንድሮው የበጋ ወራትም እያንዳንዳቸው በኩታ ገጠም እርሻ ከአንድ ሄክታር መሬት በላይ ስንዴንና ሩዝ እያለሙ እንደሚገኙ ጠቅሰው፤ ከዚህም ከአምናው የተሻለ ውጤት እናገኛለን የሚል እምነት እንዳላቸውም ተናግረዋል፡፡ 

የአመራር አባላቱ  በበጋው ወራት ከለማው የስንዴና የሩዝ እርሻ በተጨማሪ በበልግ እርሻ እየለማ ያለን የቦቆሎ ቡቃያና የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን ተዘዋውረው ተመልክተዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም