የኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ ሥራ ለተፋሰሱ ሀገራት የጋራ ልማትና ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ ነው - የናይል ተፋሰስ ኢኒሼቲቭ ዋና ዳይሬክተር

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 29/2016 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ ሥራ ለተፋሰሱ ሀገራት የጋራ ልማትና ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ በመሆኑ የሁሉንም ድጋፍ ይሻል ሲሉ የናይል ተፋሰስ ኢኒሼቲቭ ዋና ዳይሬክተር ፍሎሬንስ አዶንጎ (ዶ/ር) ተናገሩ።

የናይል ተፋሰስ ኢኒሼቲቭ ዋና ዳይሬክተር ፍሎሬንስ አዶንጎ (ዶ/ር)፤ ኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራን ጨምሮ እያከናወነች ያለው የአካባቢ ጥበቃ ሥራ የላቀ ፋይዳ ያለው መሆኑን ገልጸዋል።

የአባይ ተፋሰስ ሀገራት በየራሳቸው የአካባቢ ጥበቃ መርሃ-ግብር እያከናወኑ መሆኑን አንስተው፤ በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ተጠቃሽ ነው ብለዋል።

በየዓመቱ በቢሊየን የሚቆጠሩ ችግኞችን ከመትከል ባለፈ ለጎረቤት አገራት ጭምር ችግኞችን በመለገስ እያበረከተች ያለው አስተዋጽኦ አስደናቂ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም የኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ ሥራ ለተፋሰሱ ሀገራት የጋራ ልማትና ተጠቃሚነትን የሚያመጣ በመሆኑ የሁሉንም ድጋፍ ይሻል ሲሉ ተናግረዋል።

ኤኒሼቲቩ ተፋሰስ አቀፍ ፕሮጀክቶችን እስካሁን ገቢራዊ ማድረግ ባይችልም ሀገራት በብሔራዊ ደረጃ እያካሄዱ ያለውን የደን ልማት ያግዛል ብለዋል።

የናይል ተፋሰስ ሀገራት የሚያከናውኗቸው የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች በቀጣናው ዘላቂ የአካባቢ ስነ-ምህዳር ጥበቃ ለማድረግ የሚያግዙ መሆናቸውንም ገልፀዋል።

የናይል ተፋሰስ ኢኒሼቲቭ ይህን ጥረት ለመደገፍ የኃብት ማሰባሰብ ሥራ የሚሰራ መሆኑንም ዋና ዳይሬክተሯ አረጋግጠዋል።

የተፋሰሱ ሀገራት የኃይል ማመንጫ ግድቦችን ጨምሮ በተፋሰሱ የሚገነቡ የመሠረተ-ልማቶች ደኅንነትና የአገልግሎት ዘመን ለማራዘም የተፈጥሮ ኃብት ጥበቃ ወሳኝ ስለመሆኑም አንስተዋል።

በዚህ ረገድ 25 ዓመታትን ያስቆጠረው የናይል ተፋሰስ ኢኒሼቲቭ በተፋሰሱ ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቋቋም ይሰራል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም