ሚኒስቴሩ የዲጂታል 2025 ስትራቴጂ ውጤታማነትን ለማጠናከር በትኩረት መስራት እንዳለበት የህዝብ ተወካዮቸ ምክር ቤት አሳሰበ

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 29/2016(ኢዜአ)፦ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የዲጂታል 2025 ስትራቴጂን ከግብ ለማድረስ የህብረተሰቡን የዲጂታል አጠቃቀምና ግንዛቤ ማሳደግ ላይ በትኩረት መስራት እንዳለበት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ።   

ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው 3ኛ አመት የስራ ዘመን 25ኛ መደበኛ ስብሰባ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርን የ2016 በጀት አመት የዘጠኝ ወራት እቅድ አፈፃፀምን ገምግሟል።

ሚኒስቴሩ ለምክር ቤቱ ባቀረበው ሪፖርት ባለፉት ዘጠኝ ወራት ዲጂታል ኢኮኖሚን ለመገንባት የሚያስችሉ አምስት የትብብር ስምምነቶችን መፈጸሙን ገልጿል።

በዚህም ዘመናዊ የስታርት አፕ ከተማ ለመገንባት ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር ስምምነት መደረሱን አስታውቋል፡፡

ቀሪዎቹ አራቱ ስምምነቶች የዲጂታል 2025 ስትራቴጂን ለማሳለጥ በውጭ አገራት ካሉ ድርጅቶች ጋር የተፈፀሙ መሆናቸውን አስረድቷል።

የኢኖቬሽን ስነ-ምህዳር ለማስፋት በቅድመ ደረጃ ስታርት አፖች ሃሳባቸውን እንዲያበለፅጉ ለ558 ጀማሪ ስታርት አፖች የቢዝነስ ስልጠና እና ሜንቶሪንግ ድጋፍ መደረጉ በሪፖርቱ ተመላክቷል።

በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ችግር ፈቺ ምርምሮችን ለመደገፍ በመንግስት ትኩረት በተሰጣቸው የምርምር ዘርፎች ለሚከናወኑ 24 ምርምሮች የገንዘብና ቴክኒካል ድጋፍ መደረጉም ተገልጿል።

በምርምር የተገኙ ስምንት ቴክኖሎጂዎችን ማልማት እንዲሁም ሰባት ቴክኖሎጂዎችን ማላመድ መቻሉና የሳተላይትና ጂኦስፓሻል መረጃዎችን በማደራጀት ስድስት ተቋማትን ተጠቃሚ መደረጉም ተመላክቷል።

በዚህ ወቅት የምክር ቤቱ የሰው ሀብት ልማት፣ ስራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ነገሪ ሌንጮ(ዶክተር )ሚኒስቴሩ እቅዱን ከሰራተኞቹና ከክልሎች ጋር የጋራ በማድረግ መስራቱ እንደ ጥንካሬ የሚወሰድ ነው ብለዋል።


 

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ችግር ፈቺ ምርምሮችን መስራቱ በጥንካሬ እንደሚወሰድና የስፔስና ጂኦስፓሻል መረጃዎች ለአገራዊ ጥቅም እንዲውሉ የተሰሩ ስራዎችም የሚበረታቱ ናቸው ብለዋል።

በስታርት አፕ ላይ የተጀመሩ ስራዎች የሚበረታቱ ቢሆኑም የስራ እድል በመፍጠር ረገድ አሁንም የሚቀሩ ስራዎች መኖራቸውን አንስተዋል።

ሚኒስቴሩ የዲጂታል 2025 ስትራቴጂ ከግብ እንዲደርስና ህብረተሰቡ ቴክኖሎጂን አውቆ እንዲጠቀም ለማድረግ የግንዛቤ ስራ ላይ አተኩሮ መስራት እንዳለበት ተናግረዋል።

የአዕምሯዊ ንብረት ለአገር እድገት ወሳኝ በመሆኑ የተጀመሩ ሪፎርሞች ተጠናክረው እንዲቀጥሉም አሳስበዋል።

የኢኖቬሽን ሚኒስትሩ በለጠ ሞላ (ዶክተር )  በበኩላቸው የዲጂታል 2025 የመካከለኛ ዘመን ግምገማ መካሄዱንና ተስፋ ሰጪ ውጤቶች መኖራቸውን ማየት መቻሉን ጠቅሰዋል።


 

ዲጂታል ኢኮኖሚን ለመገንባት ዲጂታል ክህሎት ወሳኝ መሆኑን አንስተው በዲጂታል ክህሎት ልማት ላይ ከሌሎች ተቋማት ጋር በመተባበር እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

ስታርት አፖችን የሚያሰራ የህግ ማዕቀፍና የፋይናንስ ስርዓት እንዳልነበር አንስተው አሁን ላይ በተደረገው ማሻሻያ ምቹ ምህዳር በመፈጠሩ ከስራ እድልና ሀብት ፈጠራ አንፃር የተሻለ ውጤት ያስመዘግባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አስረድተዋል።

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም