በክልሎቹ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የአምራች ኢንዱስትሪውን ዘርፍ ማነቆዎችን በመፍታት ረገድ ተጨባጭ ውጤት ማስገኘቱ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሎቹ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የአምራች ኢንዱስትሪውን ዘርፍ ማነቆዎችን በመፍታት ረገድ ተጨባጭ ውጤት ማስገኘቱ ተገለጸ
ሀዋሳ/ሆሳዕና ሚያዚያ 29 / 2016 (ኢዜአ)፦ በሲዳማና በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከተጀመረ ወዲህ በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ያሉ ማነቆዎችን በመፍታት ረገድ ተጨባጭ ውጤት መገኘቱን የክልሎቹ ርዕሳነ መስተዳድሮች ገለፁ።
የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በክልሉ 'ኢትዮጵያ ታምርት' እና 'ሲዳማ ታምርት፣ እኛም እንሸምት' በሚል መሪ ሀሳብ ለኢንዱስትሪው ዘርፍ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ርብርብ ሲደረግ ቆይቷል።
በተለይ በክልሉ አምራች ኢንዱስትሪዎች የሃይል፣ የፋይናንስና የመስሪያ ቦታ እንዲሁም የመሰረተ ልማት እጥረትና የጥሬ እቃ አቅርቦት ችግር እንደነበረባቸው ጠቁመዋል።
በ'ኢትዮጵያ ታምርት' ንቅናቄ አማካኝነት እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር የተቀናጀ ጥረት በማድረግ ችግሮቹን ማቃለል መቻሉን አስረድተዋል።
የካፒታል እጥረት ላለባቸው ኢንዱስትሪዎች ከኢትዮጵያ ልማት ባንክና ከሌሎችም ተቋማት ጋር በመተባበር የብድርና የግብዓት አቅርቦት በማመቻቸት የተሻለ ስራ መስራቱን ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም ንቅናቄው ከተጀመረ ወዲህ በተለያዩ ምክንያቶች ሥራ አቁመው የቆዩ በርካታ ኢንዱስትሪዎች ማምረት መጀመራቸውን ገልጸዋል።
የገቢ ምርቶችን በአገር ውስጥ ምርት መተካት ከመቻላቸውም ባሻገር የነባር ኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም በማሻሻል ንቅናቄው በክልሉ ተጨባጭ ውጤት ማስገኘቱን አብራርተዋል።
የክልሉ መንግሥት የኢንዱስትሪ ዞን የመለየትና የማደራጀት ዝግጅት ስራዎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን አውስተዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰው በበኩላቸው፤ በክልሉ የ'ኢትዮጵያ ታምርት' ንቅናቄን በመጠቀም የአምራች ኢንዱስትሪ ልማትን ለማፋጠን ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
የክልሉ መንግስት ንቅናቄው የተጠበቀውን ውጤት እንዲያመጣ በርካታ የድጋፍና ክትትል ስራዎች ሲሰራ መቆየቱን ገልጸው፤ በዚህም አመርቂ ውጤት መመዝገቡን አስታውቀዋል።
በተለይ ለኢንዱስትሪ ልማቱ ማነቆ ሆኖ የቆየውን የኤሌክትሪክ ሀይል አቅርቦት የመፍታት ስራ በተቀናጀ መንገድ መከናወኑን አንስተዋል።
በተለይ ከውጭ ሀገር ሲገቡ የነበሩ ግበዓቶችን በሀገር ውስጥ ምርት በመተካት የውጪ ምንዛሪን ለማስቀረት ጥረት መደረጉን አመልክተዋል።
በክልሉ ንቅናቄውን ተከትሎ አምራች ኢንዱስትሪዎችን ለማስፋፋት ለኢንዱስትሪ ልማት አመቺ ቦታዎችን የመለየትና የማዘጋጀት ተግባር መከናወኑንም አቶ እንዳሻው ጠቅሰዋል።
በክልሉ የሚገኙ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የአገር ውስጥ ምርቶችን እንዲጠቀሙ አቅጣጫ ተቀምጦ እየተሰራ መሆኑንም አብራርተዋል።