በክልሉ ልማትን በዘላቂነት ለማስቀጠል ባለድርሻ አካላት ሃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል-አቶ እንዳሻው ጣሰው

ሆሳዕና፤ ሚያዚያ 29/2016 (ኢዜአ)፦ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ልማትን በዘላቂነት አጠናክሮ ለማስቀጠል ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው ገለጹ።

የክልሉን የሰላምና ጸጥታ ሥራ የሚገመግም መድረክ ዛሬ በሆሳዕና ከተማ እየተካሄደ ነው።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው በወቅቱ እንደገለጹት፣ በክልሉ ሰላምና ጸጥታ እንዲረጋገጥ ህብረተሰቡን በማሳተፍ በቅንጅት በተሰሩ ሥራዎች ውጤት ተመዝግቧል።

በአሁኑ ወቅት በክልሉ እየተረጋገጠ የመጣው ልማት የዚህ ውጤት መሆኑን ጠቁመው፣ ልማቱን በዘላቂነት አጠናክሮ ለማስቀጠል ባለድርሻ አካላት ሀላፊነታቸውን በቅንጅት መወጣት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

በተለይ የሰላምና ጸጥታ ሥራው ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆን የትምህርት ተቋማትን ጨምሮ ሌሎች አካላትን ማሳተፍ እንደሚገባም ተናግረዋል።


 

የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ተመስገን ካሳ በበኩላቸው እንዳሉት፣ በክልሉ ያለውን ሰላም አጠናክሮ ለማስቀጠል ማህብረሰቡን በማሳተፍ እየሰራ ይገኛል።

በተለያየ መንገድ ሊከሰቱ የሚችሉ የፀጥታ ችግሮችን አስቀድሞ በመለየት የቅድመ መከላከል ተግባር እየተከናወነ መሆኑንም አስረድተዋል።

መድረኩም በህብረተሰብ ተሳትፎ የቅድመ መከላከል ሥራውን የማጠናከር ዓላማ እንዳለው አመልክተዋል።

በመድረኩ በክልሉ ባለፉት ወራት በተከናወኑ የሰላምና ፀጥታ ሥራዎች ላይ በጋራ በመምከር ለቀጣይ ወራት አቅጣጫ እንደሚቀመጥ ተመላክቷል።

ለአንድ ቀን በተዘጋጀው መድረክ የክልሉ ሰላምና ጸጥታ መዋቅሮች እየተሳተፉ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም