በዞኑ በዘንድሮው የበጋ በጎ ፍቃድ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል

ደሴ ፤ሚያዝያ 29/2016(ኢዜአ) ፦በደቡብ ወሎ ዞን በዘንድሮው የበጋ በጎ ፍቃድ አገልግሎት ከአንድ ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የዞኑ ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ አስታወቀ፡፡

በመምሪያው የወጣቶች ማካተት፣ ንቅናቄና ተሳትፎ ቡድን መሪ አቶ ምስጋናው ደምሴ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በበጎ ፍቃድ አገልግሎት የዜጎችን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች ለማቃለል የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው፡፡

በዘንድሮ የበጋ ወቅትም በዞኑ 181 ሺህ 526 በጎ ፍቀደኞችን በተለያዩ የስራ ዘርፎች በማሳተፍ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በተከናወነ የበጎ ፈቃድ እንቅስቃሴም ከአንድ ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ገልፀዋል፡፡

በአገልግሎቱ እስካሁን 41 የአቅመ ደካሞችና የአረጋዊያን ቤት ጥገናና አዲስ ግንባታ፣ 158 ዩኒት ደም ልገሳ፣ 300 ኩንታል ዱቄት ለተፈናቃዮች ድጋፍ፣ ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው አልባሳትና ቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉን ተናግረዋል፡፡

እንዲሁም 600 ሄክታር መሬት ላይ አፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ፣ ከ250 ሄክታር መሬት ላይ በበጋ መስኖ የለማ ሰብል ከአረም የማጽዳት ስራ መስራት መቻሉንና ሌሎችም ተግባራት መከናወናቸውን አስገንዝበዋል፡፡

አገልግሎቱ ከጥቅምት ወር 2016 ዓ.ም ጀምሮ መከናወኑን ጠቁመው፤ እስካሁን በተከናወኑ ተግባራት ከ33 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው ተግባራትን መስራት እንደተቻለ አስረድተዋል።


 

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የወጣቶችን የማህበራዊ አገልግሎት ከማሻሻሉም በላይ የበርካታ ወገኖች ችግር እንዲቃለል እያገዘ እንደሆነም አመልክተዋል።

በዞኑ በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ በመሳተፍ ላይ ከሚገኙ ወጣቶች መካከል ወጣት አልዩ ሐሚድ እንዳለው በበጎ ፍቃድ አገልግሎት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ እንዲሁም በበጋ መስኖ የለማ የአቅመ ደካሞች ሰብልን ከአረም የማጽዳት ስራ ማከናወን ችለዋል።

በነጻ በሚሰራው የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ውስጣዊ እርካታ እንደሚሰማው ጠቅሶ፤ በክረምቱም በተለያዩ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ስራዎች በመሳተፍ ህብረተሰቡን በሚችለው ለማገዝ ዝግጁ መሆኑን ተናግሯል፡፡ 

በኩታ በር ወረዳ የ06 ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ሰዓዳ ኡመር በሰጡት አስተያየት ደግሞ ቤታቸው አርጅቶ በክረምት በዝናብ፣ በበጋ ደግሞ በፀሐይና በንፋስ ሲቸገሩ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።

ይሁን እንጂ በበጎ ፈቃደኞች ቤቴ በአዲስ መልኩ ተሰርቶልኝ ከችግሩ በመላቀቄ ተደስቻለሁ፤  አመሰግናለሁም ብለዋል፡፡

በዞኑ ባለፈው የክረምት ወቅት 488 ሺህ ወጣቶችን በበጎ ፍቃድ አገልግሎት በማሳተፍ ከ1 ነጥብ 7 ሚሊዮን የሚበልጡ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ከመምሪያው የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም