የንግዱ ማህበረሰብ በአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ተወዳዳሪ ለመሆን ቅድመ ዝግጅት ማድረግ ይጠበቅበታል - ኢዜአ አማርኛ
የንግዱ ማህበረሰብ በአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ተወዳዳሪ ለመሆን ቅድመ ዝግጅት ማድረግ ይጠበቅበታል
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 29/2016(ኢዜአ)፦ የንግዱ ማህበረሰብ ደረጃውን የጠበቀ ምርትና አገልግሎት በማቅረብ በአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ተወዳዳሪ ለመሆን ቅድመ ዝግጅት ማድረግ እንዳለበት የአዲስ አበባ ንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አስታወቁ።
ምክር ቤቱ "የኩባንያዎች ዝግጁነት ለአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና" በሚል የፓናል ውይይት እያካሄደ ነው።
የፓናል ውይይቱ ለአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና የኩባንያዎች ዝግጁነት፣ ተወዳዳሪነት፣ ከመንግስት የሚያስፈልጉ ድጋፎችና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደረገ ነው።
የአዲስ አበባ ንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት መሰንበት ሸንቁጤ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና በአህጉሪቱ ለስራ እድል ፈጠራና ከድህነት ለመውጣት ያለውን ፋይዳ ዘርዝረዋል።
ኢትዮጵያ በአለም አቀፍ ንግድ ከወሰደችው እርምጃዎች ውስጥ ነጻ የንግድ ስምምነቱን በመፈረም ቀዳሚ መሆኗ ተጠቃሽ እንደሚያደርጋት ጠቅሰዋል።
በመሆኑም ስምምነቱን ለመተግበር በግሉ ዘርፍና በመንግስት ትኩረት የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮችን ዘርዝረዋል።
ነጻ ገበያው ለኢትዮጵያ የመጀመሪያውና አዲስ ገበያ በመሆኑ የቴክኒክ ዝግጅት ማድረግ እንደሚያስፈልግ አንስተዋል።
የንግድ ማህበረሰቡ በአጠቃላይ ከመንግስትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመወያየትና መረጃ በመለዋወጥ ቅድመ ዝግጅት ማድረግ እንደሚገባው አመልክተዋል።
በተጨማሪም ደረጃውን የጠበቀ ምርትና አገልግሎትን በተሳለጠ መልኩ በማቅረብ ተወዳዳሪ ለመሆን መስራት ይጠበቅበታል ነው ያሉት።
ኢ-መደበኛ ንግድን ወደ መደበኛ ማምጣት፣ የማምረቻ ኢንዱስትሪዎችን ተወዳዳሪነት የሚቀንሱ ችግሮችን መፍታት፣ ጠንካራ የቁጥጥር ስርአት መገንባት፣ የፋይናንስ አቅርቦትን ማሻሻልና ሌሎች ጉዳዮች በመንግሥት ትኩረት ከሚሰጣቸው ነጥቦች ውስጥ ዘርዝረዋል።
የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ለአገራትና ለንግዱ ማህበረሰብ ያለው ፋይዳ፣ የኢትዮጵያ ዝግጁነት፣ የግሉ ዘርፍ ዝግጁነትና ተግዳሮቶች በሚሉ ጉዳዮች በውይይቱ ላይ በሙያተኞች ጽሁፎች ቀርበዋል።
ኢትዮጵያ ነጻ የንግድ ቀጣናውን ለመተግበር በርካታ ዝግጅቶችን እያደረገች መሆኑ ይታወቃል።
የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና በአጀንዳ 2063 ልዩ ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች ውስጥ ሲሆን የበለጸገችና አንድነቷ የተጠናከረ አህጉርን ለመፍጠር ያለመ ነው።