የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የሀገር በቀል አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም አሳድጓል- የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 29/2016 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አዳዲስ ሀገር በቀል አነስተኛና መካከለኛ  ኢንዱስትሪዎች ዘርፉን እንዲቀላቀሉ እና የማምረት አቅም እንዲጨምር በማድረግ እመርታዊ ለውጥ ማምጣቱን የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች ገለጹ።

" የኢትዮጵያ ታምርት" ንቅናቄ የኢንዱስትሪ ዘርፉ ማነቆዎችን በመፍታትና የዘርፉን እምርታ ለማሳለጥ ሚያዝያ 28 ቀን 2014 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በይፋ መጀመሩ ይታወሳል።

የሀገራዊ ንቅናቄው ዓላማ አምራች ኢንዱስትሪዎች የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች ለመፍታት፣ ለዘርፉ ዘላቂ ልማትና ተወዳዳሪነት እንዲሁም ዘርፉ ለኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግሩ ያለውን ሚና ማሳደግ ነው።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል እና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከተጀመረ ወዲህ ያመጣውን ለውጥ በሚመለከት ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)፤ መንግሥት በሀገር አቀፍ ደረጃ የአምራች ዘርፉን ለማሳደግ በአሥር ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ ትኩረት መሰጠቱን ገልጸዋል።

በተለይ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይፋ የሆነው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ፤ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ለመተካት፣ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን በጥራትና በብዛት ለማምረት፣ እንዲሁም የግብርና እና የማዕድን ምርቶች ላይ እሴት ጨምሮ ለገበያ ለማቅረብ አዲስ ምዕራፍ መክፈቱን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በማምረቻ ኢንዱስትሪው ላይ እመርታዊ ለውጥ ማምጣቱን ገልጸው፤ በተለያዩ ችግሮች ማምረት አቁመው የነበሩ ፋብሪካዎች ወደ ምርት እንዲገቡ ማድረጉን አውስተዋል።

የፋብሪካዎች ምርታማነት ማደጉን እና ትላልቅ የውጭ ኢንቨስተሮችም በማምረቻው ዘርፍ  እንዲሰማሩ ዕድል መፍጠሩን ተናግረዋል።

ክልሉ ወጣቶችን በማደራጀት ከጥቃቅን እና አነስተኛ እስከ መካከለኛ ፋብሪካዎችን በመክፈት ወደ ሥራ እንዲሰማሩ ማድረጉን ገልፀዋል።

ክልሉ በግብርና ዘርፍ ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆን የፍራፍሬ፣ ቅመማቅመም፣ ማርና እንስሳት ተዋፅኦ  እምቅ አቅም ያለው በመሆኑ፤  የአካባቢው ማኅበራት እሴት የሚጨምር የምርት ማቀነባበር ሥራን ጀምረዋል ነው ያሉት።

በዚህም ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል ከመፈጠሩም በላይ የኃብት ፈጣሪ ወጣቶች ቁጥር እያደገ መሆኑን ጠቁመዋል።


 

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በየክልሉ የሥራና የሀገር ምርትን የመጠቀም ባህል ላይ ለውጥ ማምጣቱን ተናግረዋል።

እንዲሁም መንግሥት ለአምራች ኢንዱስትሪዎች የሚያደርገውን ድጋፍና ክትትል በማሳደግ የምርት ጥራትና ተወዳዳሪነት እንዲጨምር ማድረጉን ገልፀዋል።

በክልሉም በግብርና ምርት ማቀነባበር፣ በጨርቃጨርቅና ሌሎችም ዘርፎች የተሰማሩ 74 ኢንዱስትሪዎች  ድጋፍ ተደርጎላቸው በሙሉ አቅም ወደ ማምረት መግባታቸውን ነው ያነሱት።

ርዕሳነ መስተዳድሮቹ አክለውም ሁለቱ ክልሎች በተለይ በግብርናው ዘርፍ ያላቸው እምቅ የጥሬ ግብዓት ለአምራች ዘርፉ ትልቅ ዕድል መሆኑን አውስተዋል።

በመሆኑም በቀጣይ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆን የማምረቻና የመሸጫ ቦታዎችን የማመቻቸት፣ መሠረተ-ልማቶችን የማሟላት እና የቴክኒክና የፋይናንስ አቅርቦቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አንስተዋል።

ኢንዱስትሪው ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት ጉልህ አበርክቶ እንዲኖረው በሥራ ላይ የሚገኙ አምራቾች ምርታማነትን እንዲያሳድጉ በመጠቆም፤ አዳዲስ አምራቾችም በዘርፉ እንዲሰማሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን የሁለት ዓመታት ጉዞን የሚያስቃኝ ኤክስፖ ከግንቦት 1 እስከ ግንቦት 5 ቀን 2016 ዓ.ም ለአምስት ተከታታይ ቀናት በሚሊኒየም አዳራሽ ይካሄዳል፡፡

በኤክስፖው ላይ አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎችን ጨምሮ 230 ድርጅቶች ምርቶቻቸውን ለዕይታና ለግብይት የሚያቀርቡ ሲሆን፤ የምርትና ቴክኖሎጂ ግብይት እንደሚካሄድ ይጠበቃል፡፡

ባለፉት ሁለት ዓመታት በንቅናቄው አምራች ኢንዱስትሪውን በመደገፍ በኩል የተሠሩ ሥራዎች እና አዲሱን የኢንዱስትሪ ፖሊሲ በሚመለከት ውይይትና የማስተዋወቂያ መርሃ-ግብሮች ይካሄዳሉ።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም