ቀጥታ፡

​​​​​​​የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የኢንዱስትሪ ዘርፉን ማነቆዎች በመፍታት አምራችና ተወዳዳሪ ማድረግ ያስቻለ ነው- የሶማሌ እና አፋር ክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 29/2016 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የኢንዱስትሪ ዘርፉን ማነቆዎች በመፍታት አምራችና ተወዳዳሪ ማድረግ ያስቻለ መሆኑን የሶማሌ እና የአፋር ክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች ተናገሩ።

"የኢትዮጵያ ታምርት" ንቅናቄ የኢንዱስትሪ ዘርፉ ማነቆዎችን በመፍታትና የዘርፉን እምርታ ለማሳለጥ ነበር ሚያዝያ 28 ቀን 2014 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በይፋ የተጀመረው።

ለሁለት ዓመታት የዘለቀው ሀገራዊ ንቅናቄ የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉን ውስብስብ ችግሮች በቅንጅት በመፍታት ተወዳዳሪና ምርታማ ማድረግ አስችሏል።

በዚህም ከውጭ ይገቡ የነበሩ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በማምረት ወጪን በመቀነስ የምርት ጥራትና አቅርቦትን ያሳለጠ ውጤታማ ንቅናቄ ሆኗል።

በተለይም በአርብቶ አደሮች አካባቢ ለኢንዱስትሪው ዘርፍ ጥሩ መሠረት ያኖረና ምርታማነትን ያሳደገ መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው የሱማሌ እና አፋር ክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች ገልፀዋል።

የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሀመድ፤ በክልሉ ቀደም ሲል የመልካም አስተዳደርና ሰላም ዕጦት ችግሮች ስለነበሩ በልማት የተጎዳ እንደነበር ያስታውሳሉ።

ከሀገራዊ ለውጡ በኋላ ግን ኢንቨስትመንት፣ የኢንዱስትሪና ከተማ ልማትን ጨምሮ በሌሎችም ሴክተሮች የሚታይ ውጤት የተመዘገበበት መሆኑን ገልፀዋል።

በተለይም የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በክልሉ የኢንዱስትሪ ምርታማነትና ተወዳዳሪነትን ያሳደገ ውጤታማ ስለመሆኑ አብራርተዋል። 

በዘርፉ ይስተዋሉ የነበሩ ማነቆዎችን በቅንጅት በመፍታት ምርታማ ያደረገና አዳዲስ ኢንዱስትሪዎችንም እውን ያደረገ የተሳካ ንቅናቄ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ተዘግተው የቆዩ አሥር ትልልቅ ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ መግባታቸውን ያስታወሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በአግሮፕሮሰሲንግ ዘርፍ በርካቶች እንዲሰማሩ አስችሏል ብለዋል።

የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያውም አምራች ኢንዱስትሪውና የግብርና ዘርፉ በተመጋጋቢነት ምርትና ምርታማነታቸው እንዲያድግ ማስቻሉን ጠቅሰዋል።

በቀጣይም ከውጭ የሚገቡ ተኪ ምርቶችን ማምረት ላይ የሚሰማሩ አልሚዎችን ተሳትፎ የማሳደግ ቅንጅታዊ ሥራ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጠዋል።


 

የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ፤ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የባለድርሻ አካላትን ጠንካራ የኢንዱስትሪ ልማት ቅንጅት የፈጠረና የዘርፉን ማነቆዎች የፈታ ስለመሆኑ አንስተዋል።

በክልሉ በተለያዩ ምክንያቶች ተዘግተው የነበሩ የጨውና ኬሚካል ኢንዱስትሪን ጨምሮ ከ100 በላይ አነስተኛ፣ መካከለኛና ከፍተኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ እንዲገቡ አስችሏል ብለዋል።

የኃይል አቅርቦት፣ የመሠረተ-ልማት ግንባታና የፋይናንስ አቅርቦትን ለማሟላት በአንድ ማዕከል የባለድርሻ አካላት ትብብር ለችግሮች ሁነኛ መፍትሔ መሆኑንም ለአብነት ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የአምራች የማምረት አቅም፣ ጥራትና ተወዳዳሪነትን ያሳካ ስለመሆኑም አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን መሠረት በማድረግ በዘርፉ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በመፍታት ጥሩ ምህዳርና  የገበያ ትስስር መፍጠር አሁንም ልዩ ትኩረት የተሰጠው መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የሚዳስስ እና ከ230 በላይ አምራቾች የሚሳተፉበት ኤክስፖ ከግንቦት 1 ቀን 2016 ዓ.ም ለተከታታይ አምስት ቀናት በሚሊኒየም አዳራሽ እንደሚካሄድ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም