የኮሪደር ልማት ስራውን በፍጥነት አጠናቆ ለሕዝብ ክፍት ለማድረግ በልዩ ትኩረት እየተሰራ ነው - ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር አባይ - ኢዜአ አማርኛ
የኮሪደር ልማት ስራውን በፍጥነት አጠናቆ ለሕዝብ ክፍት ለማድረግ በልዩ ትኩረት እየተሰራ ነው - ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር አባይ
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 29/2016 (ኢዜአ)፡- በአዲስ አበባ እየተከናወነ ያለውን የኮሪደር ልማት ስራ ከክረምት በፊት በፍጥነት አጠናቆ ወደ አገልግሎት ለማስገባት በተለየ ትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ የከተማዋ ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር አባይ ገለጹ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ የካቲት 15 ቀን 2016 ዓ.ም 3ኛ ዓመት 8ኛ መደበኛ ስብስባው የኮሪደር ልማት እቅድን አፅድቆ ወደ ስራ እንዲገባ ውሳኔ ማሳለፉ ይታወቃል።
ከ4 ኪሎ ፒያሳና የአድዋ ድል መታሰቢያ ዙሪያ፣ ከ4 ኪሎ አደባባይ በእንግሊዝ ኤምባሲ መገናኛ፣ ከሜክሲኮ ሳር ቤት በጎተራ ወሎ ሰፈር አደባባይ፣ ከአራት ኪሎ መስቀል አደባባይ እና ቦሌ ድልድይ፣ በመገናኛ አስከ አዲስ አፍሪካ ኮንቬንሽን/ ኤግዚቢሽን ማዕከል ስራው የሚከናወንባቸው ኮሪደሮች መሆናቸውን የከንቲባ ጽህፈት ቤት መረጃ ያሳያል።
አራዳ፣ ልደታ፣ ቂርቆስ፣ ንፋስ ስልክ ላፍቶና ቦሌ ፕሮጀክቱ የሚሸፍናቸው ክፍለ ከተሞች ሲሆኑ በሁሉም ኮሪደሮች ስኬታማ ስራዎች መከናወናቸውም ተገልጿል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከከተማ አስተዳደሩ አመራሮችና የኮሪደር ልማት ስራ አስተባባሪዎች ጋር ባሳለፍነው ሳምንት የስራ አፈጻጸም ግምገማ አድርገዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኮሪደር ልማት ስራው ስነ- ውበትን በማሳደግ፣ አረንጓዴነትን በማስፋትና መሰረተ ልማትን በማሻሻል የሕዝቡን ጤና ከመጠበቅ አልፎ የስራ ዕድሎችን መፍጠር መቻሉን አመልክተዋል።
እየተደረጉ ያሉ የጋራ ጥረቶች የአዲስ አበባን አጠቃላይ ይዞታ በማሻሻል ለሁሉም ነዋሪዎቿ ፍላጎቶች የተመቸ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር አባይ በልማት ስራው ከመንገድ ልማት ስራው ጎን ለጎን የአረንጓዴና የሕዝብ የጋራ መገልገያዎች፣ መዝናኛ ቦታዎች፣ የአውቶቢስና ታክሲ ተርሚናሎች፣ የእግረኛ መንገዶችና የእግረኛ መሿለኪያና መሸጋገሪያ ድልድዮች መካተታቸውን ለኢዜአ ገልጸዋል።
ልማቱ ከከተማዋ እቅድ ጋር በተጣጣመ መልኩ ዘመናዊ የፍሳሽ ማስወገጃ(ድሬኔጅና ስዌሬጅ) ስራ በውስጡ መያዙን አመልክተዋል።
የግንባታው አፈጻጸም በጥሩ ላይ እንደሚገኝ ነው ምክትል ከንቲባው የተናገሩት።
የኮሪደር ልማት ስራውን ክረምት ከመግባቱ በፊት በፍጥነት በአጠናቆ ለሕዝብ ክፍት ለማድረግ ሰፊ ርብርብ እየተደረገ ነው ያሉት ምክትል ከንቲባው፤ ስራው በተያዘው ፍጥነት ከቀጠለ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊያልቅ እንደሚችል አመልክተዋል።
የከተማ አስተዳደሩ አመራሮችና ለስራው የተቋቋመው አስተባባሪ ኮሚቴ ልማቱን በየጊዜው በመገምገም ስራዎችን በፍጥነት እንዲሄዱ እየሰሩ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
በልማት ስራው ለተነሱ ነዋሪዎችም የመኖሪያ ቤት ግንባታ፣ መስሪያ ቦታና ምትክ መሬት የመስጠት እንዲሁም የካሳ ክፍያ እየተፈጸመ መሆኑን አብራርተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት በቅርቡ ባደረገው 3ኛ ዓመት የስራ ዘመን 3ኛ መደበኛ ጉባኤ የከተማዋ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የኮሪደር ልማቱን አፈጻጸም አስመልክቶ ባቀረቡት ሪፖርት በኮሪደር ልማቱና በመልሶ ማልማት እንዲሁም በአረንጓዴና ከተማ ውበት ዘርፎች በአጠቃላይ በቋሚነት ለ1 ሺህ 485 እና በጊዜያዊነት ለ13 ሺህ 784 በድምሩ ለ15 ሺህ 269 ዜጎች የስራ እድል መፈጠሩን መግለጻቸው የሚታወስ ነው።
የኮሪደር ልማቱ ሲጠናቀቅ በነዚህ ቦታዎች ከመልሶ ማልማት በፊት ተፈጥሮ የነበረውን የስራ እድል በ51 መቶ እንደሚያሳድግ ጠቅሰው፤ የከተማዋን ገቢና የመኖሪያ ቤት አቅርቦት በመጨመርና በከተማው የስማርት ሲቲ አገልግሎት አሰጣጥን ለመተግበር መሰረት እንደሚጥል ተናግረዋል።