ሃብታቸውን የማስመዝገብ ግዴታ የተጣለባቸው ግለሰቦች ንብረታቸውን በቴክኖሎጂ የሚያስመዘግቡበት አሰራር  እየተዘረጋ ነው

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 29/2016 (ኢዜአ)፦  ከመንግሥትና ከሕዝብ ሃብትና ንብረት ጋር ግንኙነት ያላቸውና የፌደራል ስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ህግ የሚያስገድዳቸው ግለሰቦች ሃብታቸውን በቴክኖሎጂ የሚያስመዘግቡበትን አሰራር ለመዘርጋት እየሰራ መሆኑን የፌዴራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ገለጸ፡፡

ሙስናና ብልሹ አሰራር ልማትን በማዳከም የሀገርን የኢኮኖሚ እድገት የሚጎዳ፤ የሞራልና ሥነ ምግባር ቀውስ የሚያባብስ እንዲሁም ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር የሚያደርግ አለም አቀፍ ወንጀል ነው ፡፡

በኢትዮጵያም ችግሩን ለማስወገድ የተቋቋመውና ከለውጡ ወዲህ አገራዊ የፀረ ሙስና ትግሉን በበላይነት የመምራት ተልዕኮ በአዋጅ ቁጥር 1236/2013 የተሰጠው የፌደራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ነጻና ገለልተኛ ተቋም ነው ፡፡

ኮሚሽኑ በትውልድ ሥነ ምግባር ግንባታና በሙስና ቅድመ መከላከል ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ይገኛል ፡፡

በኮሚሽኑ የጥቅም ግጭት መከላከል ዋና መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን በላይነህ ለኢዜአ እንደገለጹት  በመንግስት ተቋማትና የልማት ድርጅቶች እንዲሁም በህዝባዊ ድርጅቶች የግልጽነትና ተጠያቂነት አሰራር  ለማስፈን እንዲሁም ሙስናን ለመከላከል የሃብት ምዝገባና ማሳወቅ መረጃ ሚናው የጎላ ነው ፡፡

የተመዘገበው ሃብት እንደ አስፈላጊነቱ  ለህዝብ ተደራሽ የሚሆንበት አሰራር መኖሩንም መቁመዋል፡፡

ኮሚሽኑ የሃብት ምዝገባና ማሳወቅ መረጃን መነሻ በማድረግ የመረጃ ትክክለኛነት የማረጋገጥ ሥራ እያካሄደ እንደሚገኝም አስታውቀዋል ፡፡

በመሆኑም በማጣራት ጊዜ በሚገኙ ግኝቶችና ከዜጎች በሚመጡ ጥቆማዎች መሰረት ለሙስና ወንጀል ምርመራና ክስ ለመመስረት የሃብት ምዝገባና ማሳወቅ መረጃ  ሁነኛ መሳሪያ ነው ብለዋል ፡፡

ተቋሙ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በፌደራል፣ በክልሎችና በከተማ አስተዳደሮች የ106 ሺህ 96 የመንግስት ሠራተኞች፣ አመራርና ተሿሚዎች ሃብት ምዝገባ ማካሄዱን አብራርተዋል ፡፡

በኢትዮጵያ የሃብት ምዝገባ ከተጀመረ ከ10 ዓመት በላይ ቢያስቆጥርም በበጀት ውስንነትና ከኦንላይን ምዝገባ ጋር በተያያዘ የሚከሰተው የሲሰተም ችግር ምዝገባው በታሰበው ልክ እንዳይሆን አድርጎታል፡፡

ከመንግስትና ከሕዝብ ሃብትና ንብረት ጋር ግንኙነት ያለው ሁሉ ሃብቱን በቴክኖሎጂ ማስመዝገብ የሚችልበትን አሰራር ኮሚሽኑ ከኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ተቋም ጋር በመተባበር በማበልጸግ ላይ ይገኛል ብለዋል ፡፡

ሲስተሙ ወደ ስራ ከገባ በኋላ ተቋሙ የተመዘገበውን ሃብት የማጣራትና ዜጎች ምንጩ ላልታወቀ ሀብት እንዳይጋለጡ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ ላይ ትኩረቱን እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም