የኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ ክፍለ ጦሮችና ሬጅመንቶች ተልዕኳቸውን በአኩሪ ሁኔታ እየፈፀሙ ይገኛሉ- ሌተናል ጄኔራል ሹማ አብደታ

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 28/2016 (ኢዜአ)፦ የኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ ክፍለ ጦሮችና ሬጅመንቶች ተልዕኳቸውን በአኩሪ ሁኔታ እየፈፀሙ እንደሚገኙ የኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ሹማ አብደታ ተናገሩ።

የኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ በግዳጅ አፈፃፀሙና በተገኘው ውጤት ላይ ውይይት ተደርጓል።

የዕዙ ክፍለ ጦሮች ፅንፈኛውን ሀይል በመደምሰስ፣ በመማረክና እጅ እንዲሰጥ በማድረግ የተሰጣቸውን ሀገራዊ ግዳጅ በተሳካ ሁኔታ መፈፀማቸውንና ታላላቅ ድሎችን ማስመዝገባቸው በውይይቱ ላይ ተገልጿል፡፡

ሠራዊቱ በላቀ ጀግንነትና ሀገራዊ ፍቅር ጠላትን በኃይል በመምታት ቆሞ መዋጋት የማይችልበት ደረጃ ላይ አድርሶታል ያሉት ሌተናል ጄኔራል ሹማ አብደታ ፤ የሠራዊቱ ጀግንነት፣ ፅናትና ቁርጠኝነት ከሀገሩ ፍቅር የመነጨ ነው ብለዋል፡፡


 

አመራሩም በሠራዊቱ ላይ መተማመንን በመፍጠር በጠላት ላይ የበላይነቱን እንዲቀዳጅ ማድረጉን ያወሱት የዕዙ አዛዥ ፤ ፅንፈኛው ኃይል በተወሰደበት ፈጣን እርምጃ ተስፋ ቆርጦ በዘረፈው የህዝብ ሀብት እርስ በእርሱ እየተገዳደለ እንደሚገኝም አብራርተዋል፡፡

ታሪካዊ ጠላቶች ከውስጥ ተላላኪ ባንዳዎች ጋር በማበር ሀገሪቱ የተፈጥሮ ሀብቷን ተጠቅማ እንዳትበለፅግና ህዝቦቿ በድህነት ውስጥ እንዲኖሩ ዕልቂት ቢደግሱም ይህንን በመቀልበስ ጠላቶቿ የሚመኟት የደከመችና የተበታተነች ኢትዮጵያን ሳይሆን የበለፀገችና ጠንካራ ኢትዮጵያን ለትውልድ ለማሻገር አስፈላጊውን ሁሉ መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ነን ብለዋል፡፡

ሁሉም አመራር ወቅታዊ ሁኔታዎችን በመረዳት ለሀገሩ እና ለህዝቦቿ ሰላም ዛሬም እንደ ትላንቱ በፅናት ያለ ዕረፍት መስራት እንዳለበት ማሳሰባቸውን የመከላከያ ሰራዊት መረጃ ያመለክታል፡፡

ዛሬም ለሀገሩ የአባቶቹን አደራ የማይዘነጋ ራሱን አሳልፎ ሀገሩን የሚያሻግር ጀግና ትውልድ አካል በመሆናቸው ኩራት እንደሚሰማቸው የገለፁት የውይይቱ ተሳታፊ አመራሮች በተላላኪነት የህዝቡን ሰላም እያወከ የሚገኘውን ፅንፈኛ ሀይል ተከታትለው በመጨረስ የህዝቡን ሰላም ለማረጋገጥ በሙሉ ዝግጁነት ላይ እንደሚገኙ ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም