ለሀገራዊ ምክክሩ መሳካት የሴቶችን እገዛና ጠንካራ ተሳትፎ የሚያጎለብቱ ስራዎች እየተከናወኑ ነው

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 28/2016(ኢዜአ)፡- ለሀገራዊ ምክክሩ መሳካት የሴቶችን እገዛና ጠንካራ ተሳትፎ የሚያጎለብቱ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን በክልሎች በአመራርነት ላይ የሚገኙ ሴቶች ገለጹ።

በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በመምከር ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታትና ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ በሂደት የተለያዩ ተግባራትን በማከናወን ላይ መሆኑ ይታወቃል።

በሂደቱ በተለይም የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪል ማኅበራት እና የተለያዩ አደረጃጀቶች እገዛና ተሳትፎ የላቀ ሚና እንዳለው ይታመናል።

በሀገራዊ ምክክር ሂደቱ በተለይም የሴቶች ተሳትፎ የሚጠበቅ በመሆኑ በዚህ ረገድ ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው በክልሎች የተለያዩ ሃላፊነቶች ላይ የሚገኙ ሴቶች ተናግረዋል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤና የሴቶች ኮከስ ሰብሳቢ አለምነሽ ይባስ፤ በሀገራዊ ምክክሩ የሴቶችን ተሳትፎ ለማጎልበት የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

ለዚህ ስራ ከተለያዩ አደረጃጀቶች የተወጣጣ ኮሚቴ ተዋቅሮ ስራ የጀመረ ሲሆን አሁን ላይ በምክክር ሂደቱ ተሳትፎ ላይ የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።

ከዞን ጀምሮ እስከታችኛው መዋቅር ለማህበረሰቡ ግንዛቤ በመፍጠር የኮሚሽኑን ስራዎች ለማሳካት እገዛ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

የአፋር ክልል ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ የሴቶች ተሳትፎና ንቅናቄ ማስፋፊያ ዳይሬክተር ፋጡማ ሃንፈሬ፤ ለሀገራዊ ምክክሩ የሴቶችን ተሳትፎ ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።


 

በሂደቱ እየተደረጉ ባሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች በርካቶች ለምክክሩ በሚችሉት ሁሉ እገዛና ተሳትፎ ለማድረግ ዝግጁነታቸውን አሳይተዋልም ብለዋል።

የጋምቤላ ክልል ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ክርሙስ ሌሮ፤ የሀገራዊ ምክክሩ ጉዳይ የሁላችንም የጋራ አጀንዳ ሆኖ በልዩ ትኩረት ተይዟል ብለዋል።


 

በምክክር ሂደቱ በክልልም ይሁን በሀገር አቀፍ ደረጃ ሴቶች ጠንካራ ተሳትፎ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም