ቀጥታ፡

የበጋ መስኖ ልማት ከምርታማነት ባለፈ የአርብቶ አደሩን የአኗኗር ዘይቤ በመቀየር ረገድ ትምህርት የተገኘበት ነው - ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 28/2016(ኢዜአ)፡- የበጋ መስኖ ልማት ከምርታማነት ባለፈ የአርብቶ አደሩን የአኗኗር ዘይቤ በመቀየር ረገድ ትምህርት የተገኘበት የልማት ስኬት መሆኑን የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ ገለጹ።

የጎርፍ አደጋ ተጋላጭነትን ለመቀነስ የሚገነቡ አነስተኛና መካከለኛ ግድቦችም ለመስኖ ልማት ሥራዎች እንዲውሉ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ፤ በግብርና እና አርብቶ አደር ልማት እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎችን በተመለከተ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

በማብራሪያቸውም የአፋር ክልል ከአርብቶ አደር ባህል ወደ ከፊል አርብቶ አደርነት በመሸጋገር ሂደት በግብርና ልማት ስኬት እየተመዘገበ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በዚህም በርካቶች በተለይም የበቆሎ፣ የጥጥ፣ የማሽላና የስንዴ ሰብል ልማት ላይ እየተሰማሩ መሆኑን ገልፀዋል።

በአፋር ክልል የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት አዲስ የግብርና ሥራ መሆኑን ተናግረው፤ ከምርታማነት ባለፈ የአርብቶ አደሩን የአኗኗር ዘይቤ በመቀየር ረገድ ትምህርት የተገኘበት የልማት ስኬት መሆኑን አንስተዋል።

የዘርፉ ልማት የክልሉን እምቅ የውሃ እና የመሬት አቅም በመጠቀም ምርታማ ያደረገና ከአርብቶ አደር ባህል ወደ ከፊል አርብቶ አደርነት በማሸጋገር ሂደት የላቀ አስተዋጽዖ እያደረገ ነው ብለዋል።

በግብርና ምርታማነት አርብቶ አደሩ የሚያገኘው ጥቅም ለግብርና መሳሪያ የሚውሉ የውሃ ፓምፖችን በመግዛት እየተጠቀሙ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በአትክልትና ፍራፍሬ ልማትም ሙዝ፣ ማንጎና የሽንኩርት ምርት ከሀገር ውስጥ ባለፈ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል።

የክልሉ የግብርና ልማት የአርብቶ አደሩን ምርታማነት በማሳደግ የተሻለ ህይወት እንዲመራ እያስቻለ መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል።

በአፋር ክልል አብዛኛው ዝቅተኛ አካባቢ ከሚኖረው የዝናብ ፍሰት በተጨማሪ ከላይኛው የኢትዮጵያ ክፍል የሚመጣው ደራሽ ጎርፍ በሚያደርሰው አደጋ በኃብት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደሚያደርስ አስታውሰዋል።

በዚህ መነሻነትም የጎርፍ አደጋን በመከላከል ለመስኖ ልማት የተገነቡት የከሰምና ተንዳሆ ግድቦች የጎርፍ አደጋ ተጋላጭነትን ለመቀነስ ጉልህ አስተዋጽዖ እያበረከቱ ነው ብለዋል።

ግድቦቹ የጎርፍ አደጋ ተጋላጭነትን ከመቀነስ ባለፈ አርብቶ አደሩ ዓመቱን ሙሉ ውሃ በቅርበት እንዲያገኝ እያስቻለ መሆኑንም አንስተዋል።

የሎጊያ ጊጋ ወንዝ በታችኛው አዋሽ ተፋሰስ ዱብቲ፣ አሳይታና አፋምቦ አካባቢዎች የሚያስከትለውን የጎርፍ ተጋላጭነት የውሃ ፍሰት ሚዛናዊነትን የሚያስጠብቅ የግድብ ግንባታ ሥራ ተጀምሯል ብለዋል።

በመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር ባለቤትነት በፌደራል መንግሥት የ10 ቢሊየን ብር በጀት በታችኛውና የላይኛው አዋሽ የጎርፍ አደጋ ተጋላጭነትን ለመቀነስ የሚሰራው የግድብ ግንባታም የአርብቶ አደሩን የግጦሽ መሬትና የሰብል ልማት ምርታማነት እንደሚያሳድግ ገልፀዋል።

በዚህም አነስተኛና መካከለኛ ግድብ ግንባታ በማከናወን በጊዜያዊነት የጎርፍ አደጋን የመከላከል በቋሚነት ደግሞ ግድቦችን የመገንባት ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በአፋር ክልል የጎርፍ ተጋላጭነትን ለመቀነስ የሚገነቡ የግድብ መሠረተ-ልማቶች ዘላቂና የተረጋጋ ኢንቨስትመንትና የግብርና ምርታማነትን ለማስቀጠል የማይተካ አስተዋጽዖ እንደሚያበረክቱ ተናግረዋል።

የጎርፍ ተጋላጭነትን የመከላከል ሥራው የመስኖ ግብርና ምርታማነትና የአርብቶ አደሩን ተጠቃሚነት በማሰናሰል ውጤታማ ሥራ እየተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም