በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በድጅታል አሰራር በታገዘ አመራርነት ወጪ ቆጣቢና የተፋጠነ አገልግሎት እየተሰጠ ነው -ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 28/2016(ኢዜአ)፡- በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በድጅታል አሰራር በታገዘ አመራርነት ወጪ ቆጣቢና የተፋጠነ አገልግሎት መሰጠት መጀመሩን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ገለጹ።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ነሐሴ 13 ቀን 2015 ዓ.ም ተመስርቶ በስሩ ስድስት የአስተዳደር ማዕከላትንና 12 ዞኖችን በማካተት በይፋ ወደ ስራ መግባቱ ይታወቃል።

ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምስረታ በኋላ እስካሁን የተሰሩ የልማት፣ የአስተዳደርና ሌሎችም ተያያዥ ጉዳዮች በተመለከተ ኢዜአ ከክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ጋር ቆይታ አድርጓል።

ከምስረታው በኋላ ክልሉን የሰላም፣ የመቻቻልና የብልፅግና ተምሳሌት ለማድረግ አመራሩ ለህዝብ ቃል ገብቶ ወደ ስራ መግባቱን አንስተዋል።

ለዚህም ችግሮችን በጋራ ለመሻገር ህዝቡንና ምሁራንን በማሳተፍ የሽግግር ጊዜና መደበኛ እቅዶች ተዘጋጅተው በአሰራር፣ አደረጃጀት፣ የሰው ኃይልና መሰል ጉዳዮች በአግባቡ እንዲሟላ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በግብርና፣ በቱሪዝም፣ በማዕድን፣ በኢንዱስትሪና ዲጅታል ዘርፍ ክልሉ ያለውን እምቅ አቅም ወደ ልማት ለመለወጥም ፍኖተ ካርታ መዘጋጀቱን አንስተዋል።

በዚህም ባለፉት ዘጠኝ ወራት በአመራሩ ጥረትና በህዝቡ የነቃ ተሳትፎ የክልሉን የልማትና የሰላም ርዕይ ለማሳካት መሰረት የጣሉ ውጤቶች ተመዝግበዋል ብለዋል።

ለህዝቡ አገልግሎትን በቅርበት ተደራሽ ለማድረግ በጥናት ላይ በመመስረት በዲላ፣ ሶዶ፣ አርባ ምንጭ፣ ካራት፣ ጂንካና ሳውላ ከተሞች ክልሉ በስድስት ማዕከላት እንዲደራጅ መደረጉን ገልጸዋል።

ማዕከላቱ እንደ አንድ ማዕከል ሆነው ለህዝቡ ወጥ እና ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲሰጡ በጥናት እና በህግ የተመሰረተ የዲጅታል አሰራር በማስቀመጥ ወደ ስራ መገባቱንም ተናግረዋል።

በስድስቱም የክልሉ ማዕከላት የሚገኙ የካቢኔ አባላትና የዘርፍ የስራ ኃላፊዎች በዲጅታል የታገዘ የአመራር ስረአት እንዲከተሉ መደረጉን ገልጸዋል።

የክልሉ መስተዳድር ምክር ቤት (ካቢኔ) አባላት በስድስቱም ማዕከላት የሚገኙ የቢሮ ኃላፊዎች በአካል መገናኘት ሳይጠበቅባቸው ወርኃዊ መደበኛ ስብሰባቸውን በቨርቹዋል የሚያካሂዱ መሆኑን ለአብነት አንስተዋል።

በዚህም የዲጅታል አመራርን በመከተል ፈጣን፣ የተቀላጠፈና ወጪ ቆጣቢ የውሳኔ አሰጣጥ እየተተገበረ ስለመሆኑ ነው የተናገሩት።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም