በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ መክረን ችግሮችን ለመፍታት በሚደረገው ጥረት የበኩላችንን ለመወጣት ተዘጋጅተናል- የእድሮች ምክር ቤት

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 28/2016(ኢዜአ)፡- በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ መክረን ችግሮችን ለመፍታት በሚደረገው ጥረት የበኩላችንን ለመወጣት ተዘጋጅተናል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማና ሀገር አቀፍ የእድሮች ምክር ቤት አመራሮች ተናገሩ።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በመምከር ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት በመሥራት ላይ ይገኛል።

በሂደቱ ከዝግጅት ምዕራፍ ጀምሮ የተሳታፊዎች ልየታ በማድረግም አጀንዳ ለማሰባሰብ የሚያስችሉ ተግባራትን ለመጀመር በሂደት ላይ መሆኑ ይታወቃል።

በእነዚህ ሂደቶች አጠቃላይ የሕዝቡ ተሳትፎና እገዛ እንዳለ ሆኖ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት፣ የሲቪል ማኅበራት ምክር ቤት፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ እድሮችና ሌሎችም አካላት ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑ ይታመናል።

ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተገናኘ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ከተማና ሀገር አቀፍ የእድሮች ምክር ቤት አመራሮች ኮሚሽኑን ከማገዝ ባለፈ በሀገራችን ጉዳይ ላይ ለመምከር ተዘጋጅተናል ብለዋል።

የአዲስ አበባ ከተማና ሀገር አቀፍ እድሮች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ታምራት ገብረማርያም፤ በምክክርና በውይይት የሀገራችንን የቆዩ ችግሮች በጋራ መፍታት የሁላችንም ኃላፊነት ሊሆን ይገባል ብለዋል።

በመሆኑም የእድሮች ምክር ቤት ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት ኮሚሽኑን በማገዝና የሕዝቡን ተሳትፎ በማጠናከር የሚቻለውን ሁሉ ለማድረግ ተዘጋጅቷል ሲሉ ተናግረዋል። 

በሀገራዊ ችግሮቻችን ላይ በጋራ መክረን ለሁላችንም የምትመች ሀገር ለመገንባት በሚደረገው ጥረት የበኩላችንን ለመወጣት ተዘጋጅተናል ሲሉም አረጋግጠዋል።

በአዲስ አበባ የየካ ክፍለ ከተማ የእድሮች ምክር ቤት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ፍቅሬ ሙላት፤ የሀገራችንን ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት ከምንም በላይ ምክክር አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም በሀገራችን ጉዳይ ላይ መክረን ለትውልዱ የምትመች ሀገር ለመገንባት ተዘጋጅተናል ብለዋል።

በአራዳ ክፍለ ከተማ የእድሮች ምክር ቤት ምክትል ሰብሳቢ ስለሺ መለሰ በበኩላቸው፤ የምክክር ጉዳይ ለሀገርም ይሁን ለሕዝብ ሁነኛ መፍትሔ በመሆኑ ሁላችንም ለዚሁ ዝግጁ መሆን ይጠበቅብናል ሲሉ ተናግረዋል።

ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት የሚጠበቅብንን ኃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ ነን ሲሉም አመራሮቹ አረጋግጠዋል። 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም