ሀዋሳ ከተማ ቅዱስ ጊዮርጊስን ከመመራት ተነስቶ በማሸነፍ ደረጃውን አሻሽሏል

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 27/2016(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 23ኛ ሳምንት ጨዋታ ሃዋሳ ከተማ ቅዱስ ጊዮርጊስን 2 ለ 1 አሸንፏል።

በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ማምሻውን በተደረገው ጨዋታ የፊት መስመር ተሰላፊው አማኑኤል ኤርቦ በ14ኛው ደቂቃ ባስቆጠረው ግብ ቅዱስ ጊዮርጊስ መሪ መሆን ችሎ ነበር።

ይሁንና ከእረፍት መልስ ኤርትራዊው አጥቂ ዓሊ ሱሌማን በ68ኛው እና የአማካይ ተጫዋቹ አማኑኤል ጎበና በ84ኛው ደቂቃ ሃዋሳ ከተማን አሸናፊ ያደረጉትን ግቦች ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።

ዓሊ በውድድር ዓመቱ ያስቆጠራቸውን ጎሎች ብዛት ወደ 13 ከፍ በማድረግ የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን አጠናክሯል።

ውጤቱን ተከትሎ ሃዋሳ ከተማ በ32 ነጥብ ከነበረበት 11ኛ ደረጃ ወደ 9ኛ ከፍ ብሏል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ በ39 ነጥብ 4ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ቀን ላይ በተደረገ የ23ኛ ሳምንት ጨዋታ መቻል ወልቂጤ ከተማን 3 ለ 1 አሸንፏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም