በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መቻል ወልቂጤ ከተማን በማሸነፍ ወደ ድል ተመለሰ 

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 27/2016(ኢዜአ)፦  በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ23ኛ ሳምንት መርሐ ግብር መቻል ወልቂጤ ከተማን 3 ለ 1 አሸንፏል። 

በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ለመቻል አጥቂው ምንይሉ ወንድሙ በ13ኛው፣ 24ኛው እና 43ኛው ደቂቃ 3 ግቦችን በማስቆጠር ሀትሪክ ሰርቷል።

የአማካይ ተጫዋቹ ጋዲሳ መብራቴ በ75ኛው ደቂቃ ለወልቂጤ ከተማ ብቸኛዋን ግብ ከመረብ አሳርፏል።

መቻል ከሶስት የሊጉ ጨዋታዎች በኋላ ወደ አሸናፊነት መመለስ ችሏል።

ውጤቱን ተከትሎ በሊጉ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው መቻል ነጥቡን ወደ 44 ከፍ በማድረግ ከመሪው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ ሶስት ዝቅ አድርጓል።

ወልቂጤ ከተማ በ16 ነጥብ በነበረበት 14ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። 

የመቻል የፊት አጥቂ ምንይሉ ወንድሙ በውድድር ዓመቱ ያስቆጠራቸውን ጎሎች ብዛት ወደ 12 ከፍ በማድረግ ተመሳሳይ የግብ መጠን ካለው የሃዋሳ ከተማው አጥቂ አሊ ሱሌማን ጋር በመስተካከል የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን በጋራ መምራት ችሏል።

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ23ኛ ሳምንት የመጨረሻ መርሐ ግብር ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሃዋሳ ከተማ ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ ይጫወታሉ።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም