የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 23ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር ዛሬ ይጠናቀቃል

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 27/2016(ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ23ኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን ውሎ ሁለት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።

በወጣው መርሐ-ግብር መሠረት መቻል ከወልቂጤ ከተማ ከቀኑ 9 ሰዓት በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።

በአሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ የሚሰለጥነው መቻል በፕሪሚየር ሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት 5 ተከታታይ ጨዋታዎች 2 ጊዜ ሲያሸንፍ 1 ጊዜ ተሸንፏል። 2 ጊዜ አቻ ወጥቷል።

በእነዚህ 5 ጨዋታዎች መቻል 5 ግቦችን ሲያስቆጥር 3 ጎሎችን አስተናግዷል።

በአሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ የሚመራው መቻል በ41 ነጥብ 2ኛ ደረጃን ይዟል።

ተጋጣሚው ወልቂጤ ከተማ ካለፉት 5 የሊግ ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው 1 ጊዜ ብቻ ነው። 2 ጊዜ ሲሸነፍ በተመሳሳይ ሁለት ጊዜ ነጥብ ተጋርቷል።

ወልቂጤ በ5ቱ ጨዋታዎች 2 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 5 ጎሎች ተቆጥረውበታል።

በሙሉጌታ ምሕረት የሚሰለጥነው ወልቂጤ ከተማ በ16 ነጥብ 14ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያው ዙር ባደረጉት ጨዋታ መቻል 2 ለ 0 ማሸነፉ አይዘነጋም።

በ23ኛ ሳምንት የመጨረሻ መርሐ-ግብር ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሀዋሳ ከተማ ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

የአምናው የሊጉ አሸናፊ ቅዱስ ጊዮርጊስ ካለፉት 5 የሊጉ ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው 1 ጊዜ ብቻ ነው። 2 ጊዜ ሲሸነፍ 2 ጊዜ ደግሞ ነጥብ ጥሏል።

ፈረሰኞቹ ባለፉት 5 ጨዋታዎች 4 ግቦችን ሲያስቆጥሩ በተመሳሳይ 4 ግቦችን አስተናግደዋል።

በአሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ የሚመራው ቅዱስ ጊዮርጊስ በ39 ነጥብ 4ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ተጋጣሚው ሀዋሳ ከተማ ባለፉት 5 የሊጉ ጨዋታዎች 2ቱን ሲያሸንፍ 2 ጊዜ ተሸንፏል። 1 ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል።

በእነዚህ 5 ጨዋታዎች 9 ግቦችን ሲያስቆጥር 8 ጎሎችን አስተናግዷል። 

ዘርዓይ ሙሉ የሚያሰለጥነው ሀዋሳ ከተማ በ29 ነጥብ 10ኛ ደረጃን ይዟል።

ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያው ዙር ባደረጉት ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ 3 ለ 0 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።

በተያያዘም ትናንት በተደረጉ የ23ኛ ሳምንት የሊጉ ጨዋታዎች ሲዳማ ቡና ወላይታ ድቻ እንዲሁም ፋሲል ከነማ ሀድያ ሆሳዕናን በተመሳሳይ 2 ለ 1 አሸንፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም