ሲዳማ ቡና በፕሪሚየር ሊጉ ደረጃውን ያሻሻለበትን ድል አስመዘገበ

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 26/2016(ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ23ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ሲዳማ ቡና ወላይታ ድቻን 2 ለ 1 አሸንፏል።

በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ በተከናወነው ጨዋታ አጥቂው ይስሐቅ ካኖ በ22ኛው እንዲሁም ጋናዊው የፊት መስመር ተሰላፊ ማይክል ኪፖርቪ በ74ኛው ደቂቃ ያስቆጠሯቸው ግቦች ሲዳማ ቡናን ሶስት ነጥብ ይዞ እንዲወጣ አድርጎታል።

ተቀይሮ የገባው የወላይታ ድቻ አጥቂ ዘላለም አባተ በ85ኛው ደቂቃ ቡድኑን ከሽንፈት ያልታደገች ግብ አግብቷል።

ውጤቱን ተከትሎ ሲዳማ ቡና በ30 ነጥብ ከነበረበት 12ኛ ደረጃ ወደ 10ኛ ከፍ ያለ ሲሆን በአንጻሩ ወላይታ ድቻ በ28 ነጥብ ከነበረበት 11ኛ ደረጃ ወደ 12ኛ ዝቅ ብሏል።

በሌላኛው የ23ኛ ሳምንት የጨዋታ መርሃ ግብር ሀድያ ሆሳዕና እና ፋሲል ከነማ ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ ይጫወታሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም