የመከላከያ ሠራዊት ፋውንዴሽን ያሥገነባቸውን የጋራ መኖሪያ ቤቶች በእጣ እንደሚያሥተላልፍ አሥታወቀ

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 26/2016(ኢዜአ)፡- የመከላከያ ሠራዊት ፋውንዴሽን ያሥገነባቸውን የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንቦት 3 ቀን 2016 በእጣ እንደሚያሥተላልፍ የፋውንዴሽኑ ዋና ሥራ አሥፈፃሚ ብርጋዲየር ጄኔራል ደረጀ መገርሳ ገለጹ።

ፋውንዴሽን የሠራዊቱን የመኖሪያ ቤት እጥረት ለመፍታት ተቋሙ ባሥቀመጠው አቅጣጫ መሠረት እየሠራ መሆኑንም አስታውቀዋል።

ከዚህ በፊት በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች 1ሺህ 236 የጋራ መኖሪያ ቤቶችን አሥገንብቶ በእጣ ለሠራዊቱ እንዳስተላለፈ ዋና ስራ አስፈጻሚው ገልጸዋል።

የመከላከያ ሠራዊት ፋውንዴሽን 128 ባለ አራት መኝታ 260 ባለ ሦስት መኝታ 480 ባለ ሁለት መኝታ 220 ባለ አንድ መኝታ በድምሩ 1 ሺህ 88 ቤቶችን በቃሊቲ እንዲሁም 128 ባለ አራት መኝታ 120 ባለ ሦስት መኝታ በድምሩ 248 ቤቶችን በኮዬ ፈጬ በአጠቃላይ 1 ሺህ 336 ቤቶችን ግንቦት 3/2016 በእጣ እንደሚያሥተላልፍ አስታውቀዋል።


 

የፋውንዴሽኑ ምክትል ሥራ አሥፈፃሚና የቤቶች ግንባታና ማሥተላለፍ ሃላፊ ኮሎኔል ታደሠ ጌታቸው በበኩላቸው በእጣ በሚተላለፉት የጋራ መኖሪያ ቤቶች 1 ሺህ 125 ከሠራዊቱ የተሠናበቱ፣ 6 ሺህ 33 በሥራ ላይ ያሉ የሠራዊት አባላት እንዲሁም 539 ሲቪል ሠራተኞች በድምሩ 7 ሺህ 697 በእጣው እንደሚካተቱ ጠቁመዋል።

ፋውንዴሽኑ በእጣ ከሚያሥተላልፋቸው ቤቶች በተጨማሪ 440 ቤቶች በመቀሌ 312 ቤቶች በባህርዳር 232 ቤቶች በሃዋሳ በድምሩ 984 ቤቶችን እያሥገነባ እንደሚገኝም ገልጸዋል።


 

ኮሎኔል ታደሠ አክለውም በአዲስ አበባ ከተማ ላፍቶ ክፍለ ከተማ 1 ሺህ 24 የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በማስገንባት ለሠራዊቱ ለማሥተላለፍ የመሠረተ-ድንጋይ መቀመጡን ጠቁመዋል።

በ2016 ዓ.ም ጥር ወር ድረስ አራት እርከን የደረሱ ሲኒየር ኮሎኔሎችና ጄኔራል መኮንኖች ሙሉ በሙሉ ያለ እጣ የጋራ መኖሪያ ቤት ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ከመከላከያ ሰራዊት ማህበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም