በሐረሪ ክልል በሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፍ  የተከናወኑ ስራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል -ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ

ሐረር፤ ሚያዝያ 26//2016  (ኢዜአ)፦  በሐረሪ ክልል በሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፍ  የተከናወኑ አበረታች ስራዎች እንዲጠናከሩ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ አሳሰቡ።

የክልሉ መስተዳድር ምክር ቤት በክልሉ በሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፍ የተከናወኑ የ2016 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ዛሬ ገምግሟል።


 

የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሔኖክ ሙሉነህ ባቀረቡት ሪፖርት በክልሉ በልማት፣ በሰላምና በሌሎች መስኮች የተከናወኑ ስራዎችን መረጃ ለማድረስ መሰራቱን  ገልጸዋል።

በክልሉ መረጃን ለማህበረሰቡ ተደራሽ በማድረግ ረገድ የክልሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽንና ብዙሃን መገናኛ እንዲሁም በክልሉ የሚገኙ አገር አቀፍ መገናኛ ብዙሃን  በማስተባበር ረገድ አመርቂ ተግባራትን ማከናወናቸውን አስታውቀዋል።

 

ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ኦርዲን በድሪ በዚሁ ወቅት  እንደተናገሩት፤ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፍ የተከናወኑ ሥራዎች የተሻሉና  አበረታች ናቸው።

በአገራዊ ጉዳዮች ላይ "ብሔራዊ መግባባት ከመፍጠርና ዴሞክራሲን ከመገንባት ረገድ የተጀመሩ ስራዎችን ማጠናከር ይገባል" ብለዋል።

ዘርፉን በማጠናከርና በማዘመን በህዝብና በመንግስት መካከል ሁነኛ የመረጃ ድልድይ ሆኖ ተግባቦትን የማሳለጥ ሥራዎች እየተካሄዱ መሆናቸውንም ርዕሰ መስተዳድሩ አመልክተዋል።

ዘርፉን በስትራቴጂክ እቅድ የመምራት፣ መረጃን ለህዝብ  ተደራሽ የማድረግ እና በመረጃ የዳበረ ማህበረሰብን የመፍጠር ስራዎች እንዲጠናከሩም አስገንዝበዋል።

በዘርፉ የስራ ተነሳሽነትን በማሳደግና ተቋማዊ ግንኙነትን በማጠናከር ውጤታማ ለመሆን እንዲሰራም አቶ ኦርዲን አሳስበዋል።

 

 

 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም