ከፈተናዎች ባሻገር . . . !

                                         ከፈተናዎች ባሻገር . . . !

                                       (በቀደሰ ተክሌ ከሚዛን አማን ኢዜአ)

በዓለም ውስጥ ሆኖ በአንዳች ምክንያት የወደቀ ይነሳል፤ የታመመ ይድናል፤ የፈረሰ ይጠገናል፤ የደከመ ይበረታል፤ የተኛ ወይም ያንቀላፋም ይነቃል። ይህን እውነት ሰው በልቡ ተስፋ አድርጎ ውሎ ያድራል።ነገን ያልማል። "ሲጨልም ይነጋል" እያለ ለራሱ ይጽናናል። መከራ ሲበዛበት "ሊነጋ ሲል ይጨልማል" በሚል አዲስ ተስፋን በውስጡ ይዘራል።

ከእነዚህ ተቃራኒ የሰው ልጅ ከህይወት ዑደት ኩነቶች ባሻገር በተለያዩ የእምነት ተቋማት አስተምህሮ ደግሞ የሞተ የሚነሳበት መንፈሳዊ ተስፋ አለ። ይህም ትንሣኤ ይባላል- ከሞት በኋላ የሚኖር ሕይወትን የሚያሳይም መነጽር።

"ትንሣኤ" ማለት የግዕዝ ቃል ሲሆን፤ ቀጥተኛ ትርጉሙ መነሳት ነው። መነሳት የሚነገረው ለወደቀ፤ ለደከመ እና ለሞተ ነው። እንዲሁም ከነበረበት ከፍ ማለት ቀና ማለት መለወጥና ወደ አዲስ መልካም ነገር መሸጋገርን ያመለክታል።

በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ትንሣኤ የሚከበረው የኢየሱስ ክርስቶስን ከሞት መነሳትን መሠረት በማድረግ ነው። ክርስቶስ በምድር ሲመላለስ የሰው ልጆች ማድረግ ስለሚገባቸው በጎ ምግባራት እርሱ በመተግበር አስተምሯል። የበጎ ተግባራት ውጤት ደግሞ ከሞት በላይ ራስን ከፍ አድርጎ በሕይወት ዙፋን ላይ መቀመጥ እንደሆነ አሳይቷል። ፍቅር እንዲጎለብት ለሌላው መኖርና አልፎም መስዋዕት መሆንን በግልጽ አንጸባርቋል።

እርሱ መልካም ነገር አድርጎ "እናንተ እንዲሁ አድርጉ" ብሏል። ለአብነትም ፍቅር በቀዳሚነት የሚጠቀስ ትምህርቱ ነው "እርስ በእርስ ትዋደዱ ዘንድ ትዕዛዜ ይህች ናት" ብሏል። ፍቅሩን ለሰው ልጆች ራሱን አሳልፎ በመስጠት ገልጧል። 

ነገ ምን እንዲያውም ከደቂቃዎችና ሰዓታት በኋላ ምን እንደሚፈጠር በማናውቀው ተገድቦና ተተምኖ በተሰጠን የህይወት ዑደት ውስጥ በምናልፋቸው የትኞቹም ጎዳናዎች ምህረትን፣ ይቅር ባይነትን ይጠየቃል። ለሰው ልጅ ለራሱም ቢሆን ቂምና ቁርሾ ያላደረበት ልብ ያስፈልገዋል። የወደደንን ወይም የሰበሰበንን ሳይሆን ተቃራኒውን የፈጸመብንን የመውደድና ፍቅርን በተግባር የማሳየት ልምምድ እንዲኖረን ያስተምራል። ይህም ከራሳችን ጀምሮ ለአካባቢያችን ሁሉ ሰላምና መረጋጋትን ይፈጥራል።  

ሌላው የተግባር ትምህርቱ ትህትና ነው። የሰው ልጆችን ለማክበር ራሱን ዝቅ አድርጓል። የደቀ መዛሙራቱን እግር ተንበርክኮ አጥቧል። "እናንተም እንዲሁ ለሌሎች አድርጉ" ሲልም አስተምሯል። የዚህ ዓይነቱ ተግባር ዛሬም በኢትዮጵያውያን እሴት ውስጥ ይስተዋላል። በትውፊት ከትውልድ ወደ ትውልድ በመተላለፉ መጥቷል።  ቤታችን የወላጆቻችንን አልፎም የመጣን እንግዳ እግር ማጠብ የመልካም ሥነ ምግባር ምገለጫችን ሆኖ ቆይቷል። ይህ እርስ በርስ መከባበር እያጠነከረ ይመጣል፤ ውሎ ሲያድርም በስነ ምግባር የታነጸ የጠንካራ ማህበረሰብ  መገለጫም ይሆናል።

ትህትና ከአንገትን ጎንበስ ብሎ ሰላምታ መሰጣጣት ብቻ አይደለም። ሌሎች የተሻሉ እንዲሆኑ ማሰብን ያካተተ ከልብ የሚፈልቅ ተግባር ነው። በትዕቢት አውቃለሁ ባይነት ሳይሆን ራስን ዝቅ በማድረገ መንፈስ የተገዛ ማንነት ማዳበርን ይጠይቃል። ድርጊት የሀሳብ ውጤት ነው። ስለሆነም እርስ በርሳችን ከቤተሰብ እስከ ማህበረሰብ እንዲሁም በስራ ቦታችን ካሉ ባልደረቦቻችንን ከልብ በመነጨ ትህትና መቀበልና ማስተናገድ አልፎም መታዘዝ ይጠበቅብናል። ይህ ነው የትህትና ጥቅ እሴቱ።

በጎነት፣ ፍቅር፣ ትህትና፣ ለጋስነትና ቅንነትን የሰው ልጅ ገንዘቡ ቢያደርግ ሞትን አሸንፎ ይከብራል። ከመውደቅ ባሻገር መነሳት አለ። ከጨለማ በኋላ ብርሃን ይኖራል። ይህም ከጽልመትና ከአስቸጋሪ ነገሮች  አልፈን ብርሃን ማየት እንደሚቻል የጸና ተስፋ በመያዝ ነጋችንን ማየት ይኖርብናል።

ትንሣኤ ደስታ ነው፥ ከድቅ ድቅ ጨለማ በኋላ የሚገኝ ልዩ ብርሃን፤ ከመቃብር በላይ የሚገኝ ሐሴት ነው። የትላንት መከራ ላይ የታነጸ ጽኑዕ ደስታ፤ የትላንት መልካም ነገርን መነሻ አድርጎ የሚገኝ ክብር ነው። የሰው ልጅ በፈተናዎች ውስጥ ሆኖ ነገን ተስፋ አድርጎ ጠንክሮ መስራት ከቻለ መልካም ነገር ሁሉ ማግኘት ይችላል። 

ዛሬም ዓለም ብዙ ውጣ ውረዶችን ታስተናግዳለች። እንደ አገር ኢትዮጵያ ብዙ ችግሮች እያጋጠሟት ነው። ችግሮቹና መከራው ማብዛቱ የነገን ትንሣኤ ለማምጣት ነው። ከፈተናዎች ባሻገር ድል አለ፤ ትንሣኤ ይገለጻል። ለዚህም ነው ምንም ፈታኝ ነገር ቢኖር፣ ችግሮች ቢደራረቡም ተግቶ ሰርቶ ወደ ብርሃኑ መውጣት ይቻላል የምን ለው።    

የትንሣኤ በዓል ከበዓል ባሻገር በበጎ እይታ በመቃኘት፣ በፍቅር በመታነጽና የቅንነት ጎዳናን በመያዝ ለአገር እና ለራሳችን ክብርን ለመጎናጸፍ ተግባራዊ ምላሽ በመስጠት መሆን አለበት።   

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም