አቶ አረጋ ከበደ ለትንሳኤ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ - ኢዜአ አማርኛ
አቶ አረጋ ከበደ ለትንሳኤ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ
ባህርዳር፤ ሚያዝያ 26/2016(ኢዜአ)፦ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ ለክርስትና እምነት ተከታዮች ለትንሳኤ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ርዕሰ-መስተዳድሩ በመልዕክታቸው ህብረተሰቡ የትንሣኤ በዓልን ሲያከብር የእርስ በእርስ የመረዳዳትና የመደጋገፍ ባህል ይበልጥ በማጎልበት ሊሆን እንደሚገባ ገልጸዋል።
ህዝበ ክርስቲያኑ በዓሉን ሲያከብር የአካባቢውን ሰላምና ደህንነቱን በማስጠበቅ መሆን እንዳለበት በመግለጽ ሃይማኖታዊ ስርዓቱ በሚያዘው መሰረት በሰላም፣ በመፈቃቀርና በደስታ ማክበር እንደሚገባም ተናግረዋል።
በዓሉን ከጥንት ጀምሮ የመጣውን የእርስ በእርስ የመረዳዳት፣ የመተጋገዝና የመደጋገፍ ባህላችንን በሚያጎልብት መልኩ ማክበር እንደሚገባም ርዕሰ መስተዳደሩ አሳስበዋል።
በየአካባቢው የሚገኙ የመንግስት አካላት፣ ባለሃብቶችና የንግዱ ማህበረሰብም ጾመው ለመግደፍ የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳት በአብሮነት መንፈስ እንዲያከብሩም አቶ አረጋ መልእክት አስተላልፈዋል።
የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ትናንት 500 አቅመ ደካሞችንና የአካል ጉዳተኞችን በመደገፍ አርዓያነቱን ማሳየቱን ጠቅሰው፤ በየደረጃው ያለው መስተዳድርም ፈለጉን ተከትሎ እንዲተገብር አስገንዝበዋል።