ቀጥታ፡

ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው ለትንሳኤ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 26/2016(ኢዜአ)፡- የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰው ለትንሳኤ በዓል ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ።

ርዕሰ መስተዳድሩ በመልካም ምኞት መልዕክታቸው ያለፉት የፆምና የፀሎት ጊዜያት በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ መንፈሳዊ ሕይወትን በማደስ ፈሪሃ ፈጣሪን የተላበሰ ስብዕናና ሞራላዊ እሴትን ለማጠናከር ጉልህ ሚና የተጫወቱ ናቸው ብለዋል።

በየእምነቶቻችን አስተምህሮዎችና ድንጋጌዎች መሠረት የምናከናውናቸው ሃይማኖታዊ ክንዋኔዎች ውስጣዊና ውጫዊ ሠላምን በማጎናፀፍ የእርስ በእርስ ትስስራችን በፍቅር፣ በመከባበርና በመቻቻል ላይ እንዲመሠረትና እንዲጠናከር ድልድይ ሆነው የሚያገለግሉ ናቸው ሲሉም ርዕሰ መስተዳድሩ በመልዕክታቸው ጠቁመዋል።

በፆሙ ጊዜያት ያጎለበትናቸው መልካም ተግባራት የአብሮነትን ድልድይ የሚያጠናክሩ፣ መልካምነትን የሚያላብሱ፣ የመተባበርና የመቻቻል ሠንሰለትን የሚያጎለብቱ በመሆናቸው የዘወትር የምግባርና የተግባር መርሆዎቻችን ሆነው እንዲቀጥሉ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል ብለዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በመልዕክታቸው በዓሉ የሐሴት፣ የበረከትና የሠላም እንዲሆን መመኘታቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም