የስቅለት በዓል በመንበረ-ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም በልዩ ልዩ ኃይማኖታዊ ስነ-ስርዓቶች ተከበረ - ኢዜአ አማርኛ
የስቅለት በዓል በመንበረ-ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም በልዩ ልዩ ኃይማኖታዊ ስነ-ስርዓቶች ተከበረ
አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 25/2016 (ኢዜአ)፦የስቅለት በዓል በመንበረ-ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም በልዩ ልዩ ኃይማኖታዊ ስነ-ስርዓቶች ተከበረ።
በአሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያሪክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ፣ የቤተክርስቲያኗ ጳጳሳት፣ ካህናት እና በርካታ ምዕመናን በተገኙበት በስግደትና በጸሎት ተከብሯል።
በዚሁ ስነ ስርአት ላይ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ባስተላለፉት መልእከት፤ የስቅለት በዓል ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ልጅ ለማዳን የተቀበለውን መከራ የሚያስታውስ መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም እለቱን ስናከብር ከራስ አልፎ ለሌሎች መኖርን፣ መከባበርን፣ መዋደድን፣ ፍፁም መልካምነትንና ልግስናን በማሳየት መሆን አለበት ብለዋል።
በመንበረ-ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም አገልጋይ ርእሰ ደብር ፍሬህይወት ምንላርግልህ፤ የስቅለት በዓል ፍቅርን፣ እርስ በእርስ መተሳሰብንና ለሌሎች መኖርን የምንማርበት ነው ብለዋል።
በመንበረ-ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም የሰንበት ትምህርት ቤት አባል ሚኒሊክ ወንድአጥር በበኩላቸው፤ ስቅለት በሰዎች ዘንድ ፍፁም መተሳሰብን መረዳዳትን እና የአንዱን ችግር መፍታት የምንችልበትን ስብእና የተማርንበት ነው ብለዋል።
በሰዎች ዘንድ መተሳሰብ ከፈጠርን ሀገር ሰላም እንድትሆን ትልቅ አቅም ይፈጥሯል ነው ያሉት።