ህብረተሰቡ በግብይት ወቅት ሊያጋጥሙ የሚችሉ ህገወጥ ድርጊቶች ራሱን ሊከላከልና ሊጠብቅ እንደሚገባ ተመለከተ - ኢዜአ አማርኛ
ህብረተሰቡ በግብይት ወቅት ሊያጋጥሙ የሚችሉ ህገወጥ ድርጊቶች ራሱን ሊከላከልና ሊጠብቅ እንደሚገባ ተመለከተ
ሀዋሳ፣ ባህር ዳር ፣ ጋምቤላ ፤ ሚያዚያ 25/2016 (ኢዜአ) ፦ ህብረተሰቡ በዓልን ተከትሎ በግብይት ወቅት ሊያጋጥሙ የሚችሉ ህገወጥ ድርጊቶችን ሊከላከልና ራሱን ሊጠብቅ እንደሚገባ የሲዳማ፣ የአማራና ጋምቤላ ክልሎች ፖሊስ ኮሚሽኖች አስገነዘቡ።
በየክልሎቹ ገበያ ስፍራ በግብይት ላይ የሀሰተኛ የብር ኖቶች ዝውውርና ምግብን ከባዕድ ነገሮች ጋር ቀላቅሎ የማቅረብ ወንጀሎች በበዓል ወቅት ከሚስተዋሉ ህገወጥ ድርጊቶች መካከል ዋናዎቹ መሆናቸው ነው የተጠቆመው።
የሲዳማ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሽመልስ ቶማስ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ህብረተሰቡ በበዓል ወቅት ግብይትን ተከትሎ ከሚያጋጥሙ ወንጀሎች ራሱን ሊከላከልና ሊጠብቅ ይገባል።
በገበያ ስፍራ ህገ-ወጦች ሀሰተኛ የብር ኖቶችን ለግብይት ለመጠቀም የሚሞክሩ ስለሚኖሩ ህብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ አሳስበዋል።
በተጨማሪም ባዕድ ነገሮችን ከምግብ ጋር በመቀላቀል ለግብይት የሚያወጡ አካላትም ሊኖሩ ስለሚችሉ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
ፖሊስ የወንጀል ድርጊቶቹን አስቀድሞ ለመከላከል ግንዛቤ የመፍጠርና የክትትልና ቁጥጥር ስራ እያከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የሚዲያ ዋና ክፍል ኃላፊ ምክትል ኮማንደር መሳፍንት እሸቴ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የትንሳኤ በዓል ህብረተሰቡ በደስታ ማሳለፍ እንዲችልና በሰላም እንዲያሳልፍ ፖሊስ አስፈላጊውን ሁሉ ዝግጅት አድርጓል።
ህብረተሳቡ በዓሉ በሰላም እንዲያሳልፍ በየደረጃው የሚገኘው የፀጥታ መዋቅር ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት የተሰጠውን ተልዕኮና ስምሪት በአግባቡ እየተወጣ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
በተለይ ህብረተሰቡ በግብይት ወቅት ከሚፈጸሙ ህገ ወጥ ድርጊቶች ራሱን እንዲጠብቅኝ አመልክተዋል።
በተለይም ከሀሰተኛ የብር ኖቶች ልውውጥ ሊያጋጥም ስለሚችል በጥንቃቄ በመመልከት ግብይቱን እንዲፈጽሙ አሳስበዋል።
በጋምቤላ ክልል ከመጪው የትንሳኤ በዓል ጋር ተያይዞ ህገ ወጥ ድርጊቶች እንዳይፈጸሙ አስፈላጊውን የክትትልና ቁጥጥር ስራ እየተከናወኑ መሆኑን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል።
ኮሚሽነር ኡሞድ ኡሞድ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ከትንሳኤ በዓል ጋር ተያይዞ በግብይት ወቅት የስርቆትና ሌሎች ወንጀሎች እንዳይፈጸም ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገ ነው።
ህብረተሰቡም ከአላስፈላጊ ወንጀሎችና ህገወጥ ተግባራት ራሱን በመጠበቅ ድርጊቱን እንዲከላከል አሳስበዋል።