በሀረሪ ክልል ሰላምና የህግ የበላይነትን ከማረጋገጥ አንፃር አበረታች ስራዎች ተሰርተዋል- የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 25/2016(ኢዜአ)፡- በሀረሪ ክልል ሰላምና የህግ የበላይነትን ከማረጋገጥ አንፃር አበረታች ስራዎች መሰራታቸውን የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ገለጸ።

የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ቶፊቅ መሀመድ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በቢሮው በተከናወኑ ስራዎች ዙሪያ በሰጡት መግለጫ በክልሉ በተሰሩ ዘርፈ ብዙ ስራዎች ሰላምን ማስቀጠል ተችሏል።

በተለይም ህዝቡን በማሳተፍና የሰላሙ ባላቤት በማድረግ በተሰራው ስራ ጉልህ ሚና አበርክቷል ብለዋል።

የክልሉ ፖሊስ የሰው ሀይሉን በማሳደግ በስነ-ምግባር የታነፀ፣ በእውቀት የበለፀገ እንዲሆን ከማስቻል አንጻር በርካታ የፖሊስ አባላትን በማሰልጠን ወደ ስራ ማሰማራት መቻሉን ጠቁመዋል።

በአንዳንድ የትራፊክ ፖሊስ አባላት ላይ የሚታየውን ብልሹ አሰራር ለመቅረፍና የቁጥጥር ስርዓቱን ለማጠናከር አዳዲስ የትራፊክ ፖሊስ አባላትን በማሰልጠን ወደ ስራ እንዲገቡ መደረጉን ገልጸዋል።

ከዚህ በተጨማሪ በተለያዩ ጊዜ ከማህበረሰቡ የሚነሱትን ቅሬታዎች መሰረት በማድረግ የፀጥታ መዋቅር የማጥራት ስራዎች ሲሰሩ መቆየቱን የገለጹት ኃላፊው በዚህም ከስራ እንዲሰናበቱ የተደረጉ የፖሊስ አባሎች መኖራቸውን ጠቅሰዋል።

እንዲሁም ቀድሞ በትራፊክ ቁጥጥር ላይ ይሰሩ የነበሩ 34 አባላት በተነሳባቸው ቅሬታ ምክንያት ከትራፊክ ቁጥጥር ስራ በማንሳት በሌሎች ክፍሎች እንዲመደቡ ተደርጓል ብለዋል።

ሚሊሺያ ኃይሉን ከማጥራት አንፃርም 69 የሚሆኑ የሚሊሻያ አባላት በፈፀሙት ጥፋት እንዲሰናበቱ መደረጉን ገልጸዋል።

የሰላም አረደጃጀቶች የማደራጀት ስራ መሰራቱን ገልጸው በአደረጃጀቶቹ አማካይነትም 4ሺህ 982 የሚሆኑ ቀላል ግጭቶችን በእርቅ እንዲፈቱ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

ህገ-ወጥ ንግድን ለመከላከል በተሰራው ስራ ከ98 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የኮንትሮባንድ እቃዎች መያዛቸውንም ገልጸዋል።

ከአጎራባች የምስራቅ ሐረርጌ ዞንና ማያ ከተማ እንዲሁም በክልሉ ከሚገኙ የፌደራል የፀጥታ ሀይላት ጋር በመቀናጀት የፀረ ሰላም እንቅስቃሴን የማክሸፍ ስራ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት መሰራቱን ጠቁመው ህገወጥ የጦር መሳሪያዎችን ለመቆጣጠር በተከናወኑ ስራዎች የተለያዩ መሳሪያዎች በቁጥጥር ስር ማዋል መቻሉን ተናግረዋል።

የበጀት ዓመቱ ቀሪዎቹ ወራት የክልሉን ሰላም ለማጎልበት የጸጥታ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ መግለጻቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም