ቀጥታ፡

የስቅለት በዓል በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን እምነት ተከታዮች ዘንድ ተከበረ

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 25/2016 (ኢዜአ)፦የኢየሱስ ክርስቶስ የስቅለት በዓል በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን እምነት ተከታዮች ዘንድ ተከበረ።

በዓሉ በልደታ ማሪያም ካቶሊክ ካቴድራል ቤተክርስቲያን በርካታ የእምነቱ ተከታዮች በተገኙበት በተለያዩ ሃይማኖታዊ ሥነ-ሥርዓት ተከብሯል።

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ ሱራፌል፤ በዚሁ ሥነ- ሥርዓት ላይ በመገኘት ባስተላለፉት መልዕክት ስቅለት ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ልጅ ከኃጢአት ለማንፃት ሲል በመስቀል ላይ የተሰቀለበት ሁነት መሆኑን ተናግረዋል።


 

የዚህም መለኮታዊ መልዕክት ማሳያነቱ ከራስ ባለፈ ለሰው ልጆች ሁሉ ዋጋ መክፈልንና የመልካምነት ሁነኛ ማሳያ መሆኑን አስረድተዋል።

የትንሳኤ በዓልም አጠቃላይ የማካፈልና የመረዳዳት መሆኑን በማንሳት፤ በዓሉን እርስ በርስ በመተሳሰብ፣ በመደጋገፍ፣ መልካምን ሁሉ በማሰብና በማድረግ ጭምር ልናከብረው ይገባል ብለዋል።


 

በልደታ ማሪያም ካቶሊክ ካቴድራል ቤተክርስቲያን ስቅለትን ሲያከብሩ ያገኘናቸው የእምነቱ ተከታዮች፤ ስቅለት አንዳችን ለሌላችን ዋጋ መክፈልን የሚያስተምር ነው ሲሉ ተናግረዋል።

በመሆኑም የስቅለትን ብሎም የትንሳኤን በዓል ስናከብር ሁላችንም ከራሳችን አልፎ ለሌሎች ማሰብንና ማድረግን ዓላማ አድርገን መሆን አለበት ብለዋል።

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም