ቀጥታ፡

ባለፉት ዘጠኝ ወራት ለ277 ሺህ ዜጎች የውጭ አገር የስራ ስምሪት እድል ተፈጥሯል-የሥራ ክህሎት ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 25/2016 (ኢዜአ)፡- ባለፉት ዘጠኝ ወራት ለ277 ሺህ ዜጎች የውጭ አገር የስራ ስምሪት እድል መፈጠሩን የሥራ ክህሎት ሚኒስቴር አስታወቀ።

በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የኢትዮጵያ የሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓት ፕሮጀክት አስተባባሪ ብርሃኑ አለቃ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ዜጎች ደህንነታቸው፣ መብትና ጥቅማቸው ተጠብቆ በውጭ አገራት የስራ እድል እንዲያገኙ የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡

ለዚህ ደግሞ መንግስት ከተለያዩ አገራት ጋር ስምምነት መፈራረሙን ተናግረው፤ ለአብነትም ከሳዑዲ አረቢያ፣ ኳታር፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ ጆርዳን እና ሊባኖስ ጋር ሕጋዊ የሥራ ሥምሪት ሥምምነት መፈረሙን ጠቅሰዋል፡፡

የስራ ስምሪት መረጃዎች በቴክኖሎጂ በመታገዝ እየተመሩ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡


 

ከዚህ አኳያ የሥራ ገበያን ዲጂታል በሆነ መንገድ ለመምራት የሚያስችል አንድ የዳታቤዝ ማዕከል ተገንብቶ ወደ ስራ መግባቱን ተናግረዋል፡፡

መንግስት ከመዳረሻ አገራት ጋር ያደረገው የሁለትዮሽ ስምምነቶች የዜጎችን ደኅንነትና መብት ከማስጠበቅ ባሻገር መልካም የአሰሪና ሠራተኛ ግንኙነት እንዲፈጠር ማድረጉንም አንስተዋል፡፡

በዚህም ባለፉት ዘጠኝ ወራትም ለ277 ሺህ ዜጎች የውጭ አገር የስራ ስምሪት እድል መፈጠሩን ተናግረዋል፡፡

ህጋዊ የስራ ስምሪቱ በቴክኖሎጂ በመታገዝ ለመምራት የተከናወኑ ስራዎች ህገ-ወጥ ደላሎችን በመከላከል ረገድ ማሻሻል እንዲመጣ ማድረጉንም ነው የገለጹት፡፡

በዚህም በቴክኖሎጂ በመታገዝ በህገወጥ መንገድ ዜጎችን የሚያዘዋውሩ ደላሎችን ለመከላከል ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ዜጎች ህጋዊ የስራ ስምሪት መንገድን እንዲከተሉ ግንዛቤ የመፍጠሩ ተግባር በስፋት እየተከናወነ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም