የኢኮኖሚ ስብራቶችን በመጠገን ዘላቂ ልማትና ቀጣይነት ያለው እድገት ለማምጣት የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ- ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የኢኮኖሚ ስብራቶችን በመጠገን ዘላቂ ልማትና ቀጣይነት ያለው እድገት ለማምጣት የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ- ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 25/2016 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያን የቆዩ የኢኮኖሚ ስብራቶች በመጠገን ዘላቂ ልማትና ቀጣይነት ያለው እድገት ለማምጣት የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው የሚቀጥሉ መሆኑን የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የበጀት ዓመቱን የመንግሥት የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ሲገመግሙ በሱፐርቪዥን ቡድን የመስክ ምልከታ እንዲደረግ አቅጣጫ ማስቀመጣቸው ይታወሳል።
በዚህም መሠረት የፌዴራል ሱፐርቪዥን ቡድን ተቋቁሞ ዋነኛ ትኩረት በተደረገባቸው የተለያዩ ዘርፎች ላይ የመስክ ምልከታ ተደርጓል።
የፕላንና ልማት ሚኒስቴር የሚያስተባብረው የፌዴራል ተቋማት ሱፐርቪዥን ቡድን የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን የሥራ እንቅስቃሴን
ጎብኝቷል።
ኮርፖሬሽኑም ለውሃ፣ ለቤት፣ ለትራንስፖርት፣ ለመስኖና ሌሎች መሠረተ-ልማቶች የግንባታ ግብዓት የሚያመርትባቸው ፋብሪካዎች፣ የመኪና እና የማሽነሪ ጋራዥ ተጎብኝቷል።
ከጉብኝቱ በኋላ ማብራሪያ የሰጡት የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር)፤ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ስብራት በመጠገን ዘላቂ ልማትና ቀጣይነት ያለው እድገት ለማምጣት እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
በተለዋዋጭና ፈታኝ በሆነው ዓለም ውስጥ ጠንካራ ኢኮኖሚ መገንባት የግድ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለዚህም ጥሩ መሠረት እየተጣለ መሆኑን ተናግረዋል።
በኮንስትራክሽንና በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ እየተከናወነ ያለው ሥራ ለዚህ ሁነኛ ማሳያ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በመስክ ጉብኝቱ የኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን የፕሮጀክት ማኔጅመንት ሥርዓት ዲጂታል መሆኑ እንዲሁም የግንባታን ወጪ ለመቆጠብ ዘመናዊ የዲዛይን ቴክኖሎጂ ተግባራዊ መሆኑን አድንቀዋል።
የተገጣጣሚ ህንፃ ግንባታ ማምረቻ ማዕከሉም መንግሥት ለጀመረው የቤት ልማት ትልቅ እገዛ የሚያደርግ ነው ብለዋል።
የተጣሉ ቁሶችን መልሶ ጥቅም ላይ በማዋል ከውጭ የሚገቡ የግንባታ ጥሬ እቃዎችን ለመተካት የተጀመረው ጥረትም ሌሎች ተቋማት ጥሩ ተሞክሮ ሊሆን ይችላል ሲሉ ተናግረዋል።
በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ከግሉ ዘርፍ ጋር በሽርክና እንዲሁም የኮንስትራክሽን ፕሮጀክቶች በንዑስ ኮንትራት ለተቋራጮች በመስጠት እያከናወነ ያለው ሥራም ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።
ኮርፖሬሽኑ በተለያዩ የአፍሪካ አገራት የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ዘርፍ ለመሳተፍ የጀመረው ጥረትም የሚደነቅና ሊበረታታ የሚገባው መሆኑን ጠቅሰዋል።
የኮርፖሬሽኑ የሥራ እንቅስቃሴዎች የሀገርን ሁለንተናዊ እድገት የሚያፋጥን በመሆኑ የመንግሥት ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የኮንስትራክሽን ሥራዎች ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር መስፍን ነገዎ፤ የኮርፖሬሽኑ ሥራዎች ኃብትን መፍጠር፣ መግራትና መምራት እንደሚቻል ጥሩ ማሳያ መሆኑን ገልፀዋል።
የህንፃ መረጃ ሞዴሊንግ (BIM) ተግባራዊ ማድረግ መቻሉ ደግሞ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን በአግባቡ መቆጣጠር የሚያስችል ስለመሆኑ አስረድተዋል።
የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ዮናስ አያሌው፤ ኮርፖሬሽኑ ቀደም ሲል የዕዳ ጫና እና ሌሎችም ችግሮች እንደነበሩበት አስታውሰው፤ በለውጡ የሪፎርም ሥራዎች ወደ ትርፋማነት መሸጋገሩን ተናግረዋል።
በዚህም መሠረት በ2016 ዓ.ም ዘጠኝ ወራት ብቻ 850 ሚሊየን ብር ትርፍ ማስመዝገቡን ጠቅሰው፤ በቀጣይ አምስት ዓመት ዓመታዊ ገቢውን 100 ቢሊየን ብር ለማድረስ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
በ20 የአፍሪካ ሀገራት ቅርንጫፍ በመክፈት በምህንድስና፣ በኮንስትራክሽን እና በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ምርጥ ኩባንያ ለመሆን እየሰራ ስለመሆኑም ገልፀዋል።