ቀጥታ፡

የፕሪሚየር ሊጉ መሪ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከኢትዮጵያ ቡና የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ሆኗል

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 25/2016 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መሪ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከኢትዮጵያ ቡና የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል። 

የሊጉ 23ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ውሎ የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ከምሽቱ 12 ሰዓት በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይካሄዳል።

ዘንድሮ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ያደገው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እስካሁን ባደረጋቸው 22 ጨዋታዎች 14ቱን ሲያሸንፍ 4 ጊዜ ተሸንፏል። በቀሪው 4 ጨዋታ አቻ ወጥቷል።

በ22 ጨዋታዎች 40 ጎሎችን ሲያስቆጥር 21 ግቦችን አስተናግዷል።

በአሰልጣኝ በፀሎት ልዑልሰገድ የሚመራው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባደረጋቸው ያለፉት 5 ተከታታይ ጨዋታዎች በ3ቱ ሲያሸንፍ 1 ጊዜ ተሸንፏል። 1 ጊዜ አቻ ወጥቷል።

በ5ቱ ጨዋታዎች 5 ጎሎች ተቆጥረውበት፣ 9 ጎሎችን አስቆጥሮ አጠቃላይ በሊጉ 46 ነጥቦችን በመሰብሰብ የሊጉ መሪ መሆን ችሏል።

ኢትዮጵያ ቡና በበኩሉ በሊጉ እስካሁን ባደረጋቸው 22 ጨዋታዎች 9 ጊዜ ሲያሸንፍ በ6ቱ ሽንፈት ገጥሞት 7 ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል።

በአሰልጣኝ ነጻነት ክብሬ የሚመሩት ቡናማዎቹ በ22 ጨዋታዎች 31 ግቦችን ሲያስቆጥሩ 23 ጎሎችን አስተናግደዋል።

ቡናማዎቹ በ34 ነጥብ 6ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያው ዙር ባደረጉት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 2 ለ 1 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።

በሌላኛው የ23ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ኢትዮጵያ መድን ከሀምበሪቾ ከቀኑ 9 ሰዓት ሰዓት ላይ ይጫወታሉ።

በአሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ የሚመራው ኢትዮጵያ መድን ባለፉት 5 የሊግ ጨዋታዎች ሳይሸነፍ 2 ጊዜ አሸንፎ 3 ጊዜ አቻ የወጣ ሲሆን በሊጎ በሰበሰባቸው በ22 ነጥቦች 13ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

በብሩክ ሲሳይ የሚሰለጥነው ሀምበሪቾ ካለፉት አምስት የሊግ ጨዋታዎች 4 ጊዜ ሲሸነፍ 1 ጊዜ ነጥብ ተጋርቷል።

በ8 ነጥብም የመጨረሻውን 16ኛ ደረጃ ይዟል።

ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያው ዙር ባደረጉት ጨዋታ ኢትዮጵያ መድንብ 2 ለ 0 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።

በተያያዘም ትናንት በተደረጉ የ23ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ጨዋታዎች አዳማ ከተማ ሻሸመኔ ከተማን እንዲሁም ባህር ዳር ከተማ ድሬዳዋ ከተማን በተመሳሳይ 1 ለ 0 አሸንፈዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም