የፋሲካን በዓል ምክንያት ያደረገ አገር አቀፍ የንግድ ትርኢትና ባዛር በድሬዳዋ ከተማ ተከፈተ - ኢዜአ አማርኛ
የፋሲካን በዓል ምክንያት ያደረገ አገር አቀፍ የንግድ ትርኢትና ባዛር በድሬዳዋ ከተማ ተከፈተ
ድሬዳዋ ፤ ሚያዝያ 24/2016 (ኢዜአ)፡- የሴቶች አደረጃጀቶችን አቅም ለማሳደግ እና የገበያ ትስስርን ለመፍጠር የሚያግዝ ሀገር አቀፍ የንግድ ትርዒትና ባዛር በድሬደዋ ከተማ ዛሬ ማምሻውን ተከፍቷል።
ከ50 በላይ የኢንዱስትሪ ውጤቶችን ይዘው የቀረቡ ተቋማትና ድርጅቶች በባዛሩ ላይ ተሳትፎ እያደረጉ መሆኑም ተገልጿል።
የፋሲካ በአልን ምክንያት በማድረግ ማምሻውን የተከፈተውን የንግድ ትርኢትና ባዛር ያዘጋጁት የኢትዮጵያ ሴቶች ፌደሬሽን ከድሬዳዋ ሴቶች ፌደሬሽን ጋር በመተባበር ነው።
የንግድ ትርዒትና ባዛሩን በይፋ የከፈቱት ደግሞ የድሬደዋ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ፈትሂያ አደን፣ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር እና የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ወይዘሮ አስካለ ለማ ናቸው።
በዚሁ ጊዜ ወይዘሮ አስካለ ለማ እንደተናገሩት፤ የንግድ ትርኢትና ባዛሩ አላማ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የሴቶች አደረጃጀቶችንና ፌደሬሽኖችን የገቢ አቅም ማሳደግና ማስፋትን ታሳቢ ያደረገ ነው።
በተጨማሪም በየዘርፉ የተሰማሩ ሴቶችን ከገበያው ጋር በማስተሳሰር በልማቱ ላይ ያላቸው ተሳትፎ እንዲጨምር ለማድረግ መሆኑንም ገልፀዋል ።
የድሬደዋ አስተዳደር ከንቲባ እና የለውጡ አመራሮች የንግድ አውደ ርዕዩ ስኬታማ እንዲሆን እና በአስተዳደሩ የሚገኙ የሴቶች ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት እንዲጎለብት እያደረጉ የሚገኙትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጠይቀዋል።
''የሴቶች አደረጃጀቶች የራሳቸው መታደዳሪያ በጀት ስለሌላቸው የገቢ ምንጫቸውን ከአባላት መዋጮ ባሻገር ያሉ አማራጮችን አሟጦ ለመጠቀም የሚያስችል ስራ በትኩረት እየተሰራ ነው'' ብለዋል።
ከነዚህ ስራዎች ጎን ለጎን ሴቶች ዘላቂ ሰላም፣ ልማትና የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታን ለማጠናከር እያደረጉ የሚገኙት ተሳትፎ እየጎለበተ እንደሚገኝ አውስተዋል።
የአገራዊ የምክክር ኮሚሽን ተልዕኮ እንዲሳካም የሴቶች አበርክቶ እየጨመረ መምጣቱን አክለዋል።
በጅግጅጋ ተጀምሮ በድሬደዋ የቀጠለው እና በ24 የአገራችን ከተሞች የሚካሄደው የንግድ ትርኢትና ባዛር በየከተሞቹ የሚገኙትን የሴቶች ፌደሬሽኖችን አቅም ለማሳደግ ሚናው የጎላ መሆኑንም ፕሬዚዳንቷ ገልጸዋል።
"ትርኢቱ ሸማቾችን ከአምራቾች በማገናኘት የገበያ ተስስርን ለማጠናከርም ያግዛል" ብለዋል።
የድሬደዋ ሴቶች ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሁክሚያ መሐመድ በበኩላቸው ፌደሬሽኑ ያዘጋጀው አገር አቀፍ የንግድ ትርዒትና ባዛር የሚፈለገውን ውጤት እንዲያመጣ አስፈላጊውን ድጋፍ እናደርጋለን ብለዋል።
ዛሬ በድሬዳዋ ሳብያን ሜዳ የተከፈተው አገር አቀፍ የንግድ ትርዒትና ባዛር እስከ ግንቦት 10 እንደሚቆይም የተገኘው መረጃ ያመለክታል።