ቀጥታ፡

የጸሎተ ሐሙስ  "ሕፅበተ እግር" ስነ ስርዓት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እና በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ተከበረ

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 24/2016(ኢዜአ)፡- የኢየሱስ ክርስቶስ የትህትና እና አክብሮት መገለጫ የሆነው የጸሎተ ሐሙስ ‘ሕፅበተ እግር" ስነ ስርዓት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እና በኢትዮጵያ ካቶሊካውያን አማኞች ዘንድ ተከብሯል።

ዕለቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያሪክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ፣ የቤተክርስቲያኗ ጳጳሳት፣ ካህናት እና ምእመናን በተገኙበት በመንበረ-ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ቤተክርስቲያን ተካሂዷል።

የሃይማኖቱ ተከታዮችም ኢየሱስ ክርስቶስ በፍጹም ትሕትና የደቀ መዛሙርቱን እግር ያጠበበት፣ ከሐዋርያት ጋር ግብር የገባበትን የጸሎተ ሐሙስ ዕለት በቅዳሴ፣ በስግደት እና በሕፅበተ እግር አክብረዋል።

በቤተ ክርስቲያኗ አስተምህሮ ካህናት አባቶች በዕለተ ሐሙስ በዕውቀት፣ በዕድሜ፣ በክብር፣ በስልጣን ትልቅ ነኝ ሳይሉ ከዲያቆናት እስከ ምዕመናን ድረስ ዝቅ ብለው እግር በማጠብ የክርስቶስን ትህትና በተግባር ይሰብካሉ።

በዛሬው ዕለትም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ የጳጳሳቱን እግር በማጠብ የኢየሱስ ክርስቶስ ትህትናና አክብሮት መገለጫ የሆነውን የ“ሕጽበተ እግር” ስነ ስርዓት አከናውነዋል።

በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ገዳም የስብከተ ወንጌል ፀሐፊ ዲያቆን ነብዩ ኤልያስ ለኢዜአ እንደገለጹት የዛሬዋ ዕለት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ትልቅ ስፍራ የሚሰጣት ናት።


 

ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህች ዕለት የሐዋርያቱን እግር በፍጹም ትህትና ዝቅ ብሎ በማጠብ ፍቅርን እና ትህትናን ማስተማሩን እና የኦሪት መስዋዕትን በመሻር የሐዲስ መስዋዕትን መስራቱንም ገልጸዋል።

በመሆኑም ማህበረሰቡ የዕለቱን ሃይማኖታዊ አስተምህሮ በተግባር በመላበስ እንግዳ ተቀባይነትን፣ ፍቅርን፣  ሰዎችን ማክበርን እና ትህትናን የዘወትር ተግባሩ ሊያደርግ እንደሚገባም ተናግረዋል።

በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የጸሎተ ሐሙስ "ሕፅበተ እግር" ስነ ስርዓትን በእግር ማጠብና በቅዱስ ቁርባን ስነ ስርዓት አክብራለች።

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነ ኢየሱስ እንደገለጹት፥ ጸሎተ ሐሙስ ኢየሱስ ክርስቶስ ዝቅ ብሎ የደቀ መዛሙርትን እግር በማጠብ ያስተማረውን ትህትና ለምዕመናን በተግባር በማሳየት የሚሰበክበት ዕለት ነው።


 

የሃይማኖቱ ተከታዮች ከፈጣሪ የተማሩትን ትህትና በህይወታቸው በመግለጥ  ፍቅርን፣ ቅንነትንና አክብሮትን በተግባር እንዲኖሩም ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነ ኢየሱስ አባታዊ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም