የኢትዮጵያ እና የኢራቅ ረዥም ዘመናት ያስቆጠረን የሁለትዮሽና ዘርፈ ብዙ ግንኙነት  ለማጠናከር ይሰራል 

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 24/2016(ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያ እና የኢራቅ ረዥም ዘመናት ያስቆጠረን የሁለትዮሽና ዘርፈ ብዙ ግንኙነትን  ለማጠናከር እንደሚሰሩ በኢራቅ  የኢትዮጵያ አምባሳደር ሰኢድ ሙሁመድ ጅብሪል  ገለጹ ።

በኢፌዴሪ ልዩ መልዕክተኛ እና ባለሙሉሥልጣን አምባሳደር ሰኢድ ሙሁመድ ጅብሪል (ዶ/ር) በባግዳድ በሚገኘው ሰላም ቤተ መንግሥት በተካሔደው ሥነ-ሥርዓት ላይ በመገኘት የሹመት ደብዳቤያቸውን ለኢራቅ ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት አብዱላጢፍ ጀማል ረሽድ (ዶ/ር) አቅርበዋል።
 
አምባሳደሩ በወቅቱ እንዳሉት  በኢትዮጵያ እና ኢራቅ ረዥም ዘመናት ያስቆጠረውን የሁለትዮሽና ዘርፈ ብዙ ግንኙነት በፖለቲካ፣በኢኮኖሚ፣በኢነርጂ ፣ባህልና ቱሪዝም ዘርፍ ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።


 

የኢራቅ መንግስት በድጋሜ በኢትዮጵያ  ኤምባሲውን ለመክፈት ላደረገው ተነሳሽነት ምስጋና በማቅረብ የኢትዮጵያ መንግስት ጥያቄውን መቀበሉንና አስፈላጊውን እርዳታ ለማድረግ ያለውን ዝግጁነትም አብራርተዋል።

አምባሳደሩ ፕሬዝዳንት ሳህለ-ወርቅ ዘውዴ ለኢራቁ ፕሬዝዳንት አብዱላጢፍ ጀማል ረሽድ(ዶ/ር) የላኩትን መልዕክትና  የመልካም ምኞት አድርሰዋል።

የኢራቁ ፕሬዝዳንት በበኩላቸው ኢራቅ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት  የሁለትዮሽ እና በባለብዙ ወገን  ትብብር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል  አረጋግጠዋል።

የኢራቅ መንግስት በኢትዮጵያ በድጋሜ ኤምባሲውን ለመክፈት አስፈላጊውን ዝግጅት ማጠናቀቁንና በኢትዮጵያም በኩል ተቀባይነትን ማግኘቱን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም