የባህር ዳር ከተማን ፅዳትና ውበት የመጠበቅ  ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ

ባህር ዳር ፤ ሚያዝያ 24/2016(ኢዜአ)፡- የባህር ዳር ከተማን ጽዳትና ውበት በመጠበቅ ለኑሮ ተስማሚ ለማድረግ የተጀመሩ ስራዎች ህብረተሰቡን በማሳተፍ ተጠናክረው  እንደሚቀጥል የከተማ አስተዳደሩ አስታወቀ።

"የአካባቢ ብክለት ይብቃ ውበት ይንቃ" በሚል መሪ ሀሳብ የአካባቢ ብክለት መከላከል የንቅናቄ መድረክ ዛሬ በባህር ዳር ከተማ  ተካሂዷል።

የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ አቶ አስሜ ብርሌ እንዳሉት፤ የአካባቢን ብክለት ለመጠበቅ በተቀናጀ መንገድ መስራት ይገባል።


 

በተለይ የኢንዱስትሪ ፍሳሽና ደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ የአካባቢን ስነ-ምህዳር ከመበከል ባለፈ በሰውና በእንስሳት ላይ ሊያደርስ የሚችለው የጤና መታወክ ከፍተኛ መሆኑን አመልክተዋል።

በመሆኑም የአካባቢ ብክለትን በዘላቂነት ለመከላከልና  የከተማውን ጽዳትና ውበት ለመጠበቅ እየተደረገ ያለው ጥረት ህብረሰተቡን ባሳተፈ መልኩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

ሌሎች ባለድርሻ አካላትም ተገቢውን እገዛ ሊያደርጉ እንደሚገባ አመልክተዋል። 


 

የከተማ አስተዳደሩ የአካባቢ ጥበቃ ፅዳትና ውበት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብርሃም ወርቁ በበኩላቸው እንዳሉት፤ በተለይ ከከተማዋ የሚለቀቁ ፍሳሽና የደረቅ ቆሻሻዎች በጣና ኃይቅና በአባይ ወንዝ ላይ ብክለት እንዳይደርስ በቅንጅት ይሰራል ብለዋል።

በየቦታው የሚጣሉ ፕላስቲኮችን በመሰብሰብ እሴት ጨምረው ለገበያ የሚያቀርቡ 13 ኢንተርፕራይዞች ተቋቁመው እየሰሩ መሆናቸውን ጠቁመው፤ "ጥረታቸውን የማገዝ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል" ብለዋል።

በአካባቢ ላይ ከፍተኛ ብክለት የሚያስከትለውንና በየቦታው የሚጣለውን ፕላስቲክ በአግባቡ ማስወገድ እንደሚገባ የገለፁት ደግሞ የክልሉ አካባቢና ደን ጥበቃ ባለስልጣን ምክትል ዳይሬክተር አቶ በልስቲ ፈጠነ ናቸው።


 

በየአካባቢው የሚጣል ፕላስቲክ ለረጅም ዘመን ሳይበሰብስ በመቀመጥ ለጉዳት የሚያጋልጥ መሆኑን ጠቅሰው፤ "ተቀናጅቶ መከላከል የሁሉም አጀንዳ ሊሆን ይገባል" ብለዋል።

በንቅናቄ መድረኩ የክልል፣ የከተማ አስተዳደሩና የክፍለ ከተማ አመራር አባላትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።    

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም