በአዲስ አበባ በሚካሄደው የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ 200 አምራች ኢንዱስትሪዎች ይሳተፋሉ - ኢዜአ አማርኛ
በአዲስ አበባ በሚካሄደው የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ 200 አምራች ኢንዱስትሪዎች ይሳተፋሉ
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 24/20216 (ኢዜአ)፦ ከግንቦት 1 /2016 ጀምሮ ለአምስት ተከታታይ ቀናት በአዲስ አበባ በሚካሄደው የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ 200 አምራች ኢንዱስትሪዎች እንደሚሳተፉ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ኤክስፖው የኢንዱስትሪዎችን የምርታማነት አቅም በማሳየት 3 ቢሊየን ብር የሚገመት የገበያ ትስስር መፍጠር እንደሚያስችል ተገልጿል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ታረቀኝ ቡሉልታ፤ የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖን አስመልክተው ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫውም ከግንቦት 1 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ለአምስት ተከታታይ ቀናት በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ ለሚካሄደው የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ በቂ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።
የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገራት አምራች ኢንዱስትሪዎች በሚሳተፉበት ኤክስፖ መክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ላይ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ ዓለም አቀፍ ጎብኝዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እንደሚታደሙ ገልፀዋል።
መድረኩም የተኪ እና የወጪ ምርት ኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም የደረሰበትን ደረጃ የሚያሳዩ 200 አነስተኛ፣ መካከለኛ እና ከፍተኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች እንደሚሳተፉ ተናግረዋል።
ከእነዚህ ውስጥም 80 የሚሆኑት አነስተኛና መካከለኛ እንዲሁም 120 የሚሆኑት ከፍተኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች መሆናቸውን አስታውቀዋል።
በኤክስፖው የቆዳና ቆዳ ውጤቶች፣ የጨርቅና አልባሳት፣ የምግብና መጠጥ፣ የእንጨትና እንጨት ውጤቶች፣ የኬሚካልና ግንባታ መሳሪያ እቃዎች፣ አውቶሞቢልንና ማሽነሪ፣ የኤሌክትሮኒክስና ኤሌክትሪካል አምራች ኢንዱስትሪዎች ምርትና አገልግሎታቸውን ያሳያሉ ብለዋል።
የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ የሀገር ውስጥና የውጭ ጎብኝዎችን፣ በአዲስ አበባ የሚገኙ ኤምባሲዎችን ጨምሮ ከ50 ሺህ በላይ ሰዎች በጉብኝቱ እንደሚሳተፉ ገልፀዋል።
የከፍተኛ ትምህርት፣ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት እና የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ኤክስፖውን አንደሚጎበኙ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ የምርት ሂደት የሚታይበትና የ3 ቢሊየን ብር የገበያ ትስስር የሚፈጠርበት መድረክ እንደሚሆንም አስረድተዋል።
ጎን ለጎንም የኢትዮጵያን የአምራች ኢንዱስትሪ ታሪካዊ ሂደት የሚያስቃኝ የፎቶ ኤግዚቢሽን የሚካሄድ መሆኑን ጠቁመው፤ 16 ኢንዱስትሪዎች በኤክስፖው ላይ የምርት ሂደታቸውን እንደሚያሳዩ ተናግረዋል።
በአምስት ቀናቱ የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ የፓናል ውይይት በማካሄድ በማጠቃለያ መርሃ-ግብሩ ላይ በወጪና ተኪ ምርት የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ አምራቾች ዕውቅና እንደሚሰጥ ተገልጿል።
የአምራች ኢንዱስትሪ ማነቆን መፍታት፣ ለዘላቂ ልማትና ተወዳዳሪነት ምቹ ሁኔታ መፍጠርና ለኢኮኖሚው መዋቅራዊ ሽግግር አስተዋጽዖ እንዲያደርግ ማስቻል የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ዋነኛ ዓላማዎች መሆናቸው ይታወቃል።