በቀጣይ አስር ቀናት የሚጠበቀው እርጥበት የግብርና ተግባራትን ለማከናወን የጎላ ጠቀሜታ ይኖረዋል - የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 24/2016(ኢዜአ)፡- በቀጣይ አስር ቀናት የሚጠበቀው እርጥበት የበልግም ሆነ በከፊል የመኸር ወቅት የግብርና ተግባራትን ለማከናወን የጎላ ጠቀሜታ እንደሚኖረው የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ገለጸ።

ኢንስቲትዩቱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ በቀጣይ ቀናት ወቅታዊው ዝናብ ቀስ በቀስ ከበልግ አብቃይ የኢትዮጵያ ክፍሎች እየቀነሰ በመሄድ ወደ ደቡብ ምዕራብና ምዕራብ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ እንደሚስፋፋ ጠቁሟል።

በተጠቀሰው ጊዜ የሚጠበቀው እርጥበት የበልግም ሆነ በከፊል የመኸር ወቅት የግብርና ተግባራትን ለማከናወን የጎላ ጠቀሜታ አለው ብሏል።

ቀደም ብለው ለተዘሩ የበልግና የረጅም ጊዜ የመኸር ሰብሎች፣ ለቋሚ ተክሎች፣ በከተማ ግብርና ለሚለሙ የጓሮ አትክልቶች እንዲሁም ለተለያዩ እጽዋት የውሃ ፍላጎት መሟላት ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለውም ገልጿል።

የሚጠበቀው እርጥበት ለአርብቶ አደርና ለከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎች የግጦሽና የመጠጥ ውሃ አቅርቦትን ለማረጋገጥ ወሳኝ ሚና እንዳለውና ይህንን መልካም አጋጣሚ የሚመለከታቸው አካላት እንዲጠቀሙበት ኢንስቲትዩቱ አሳስቧል።

በእርጥበቱ የሚገኝ የዝናብ ውሃም ለአርብቶ አደርና ለከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎች የእንስሳት መኖን በበቂ ሁኔታ ለማሰባሰብና በተገቢው ቦታ ለማከማቸት እንደሚያግዝም ነው ያስታወቀው።

በሌላ በኩል በአንዳንድ አካባቢዎች የሚጠበቀው ከፍተኛ መጠን ያለው እርጥበትና የሚኖረው ዝናብ ለጎርፍ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ላይ በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ ጉዳት እንዳያስከትል የቅድመ ጥንቃቄ ተግባራትን ማከናወን እንደሚያስፈልግም በመግለጫው ላይ ተጠቁሟል።

መደበኛ የውሃ መፋሰሻዎችን የማጽዳት፣ የጎርፍ መቀልበሻ ቦዮችን የማዘጋጀትና ለጎርፍ ተጋላጭ የሆኑ የወንዝ ዳርቻዎችን መገደብ እንደሚያስፈልግ ነው ኢንስቲትዩቱ የገለጸው።

በተለይም ተዳፋታማና ለጎርፍ ተጋላጭ በሆኑ ማሳዎች ላይ ሰብሎች በጎርፍ ተጠርገው እንዳይወሰዱ የጎርፍ መቀልበሻ ቦዮችን ማዘጋጀት እንደሚገባም እንዲሁ።

በእርጥበቱ ምክንያት የሚኖረው ምቹ የአየር ሁኔታ ለበረሃ አንበጣ መራባትና መሰራጨት ምቹ ሊሆን ስለሚችል የሚመለከታቸው አካላት አስፈላጊውን ክትትልና ቁጥጥር እንዲያደርጉ ኢንስቲትዩቱ አሳስቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም